Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል በሄክታር የሚገኘው ምርት 32 ኩንታል ደርሷል – ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰራው ስራ በሄክታር የሚገኘው ምርት 32 ኩንታል ደርሷል አሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ።

ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በገጠር ልማት ዘርፍ የተገኘውን ለውጥ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ የአማራ ክልል ለችግር ሳይበገር በርካታ የልማት ስራዎችን አከናውኗል፡፡

ክልሉ አጋጥሞት የነበረውን የሰላም እጦት ተቋቁሞ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በሌማት ትሩፋትና ሌሎች ኢንሼቲቮች አበረታች ውጤት አምጥቷል ብለዋል።

የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰራው ስራ በሄክታር ይገኝ የነበረውን 28 ኩንታል ወደ 32 ኩንታል ማሳደግ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

በተያዘው የምርት ዘመን እስካሁን 6 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ መሰራጨቱን ጠቅሰው፤ በግብርና ሜካናይዜሽን፣ በእንስሳት ሃብት ልማትና በዘመናዊ መስኖ አውታር ግንባታ ዘርፎች አበረታች ለውጥ ታይቷል ብለዋል፡፡

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ለደን እና ፍራፍሬ ችግኞች ልዩ ትኩረት በመስጠት ተጠቃሚነትን ከተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ልማት ጋር በማስተሳሰር ውጤታማ ስራ መሰራቱን ጠቅሰዋል፡፡

በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተበሰረው የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ የክልሉን ግብርና ለማሳደግ ትልቅ እድል ይዞ ይመጣል ብለዋል።

ፋብሪካ በክልሉ ያለውን የግብዓት ፍላጎት ለመሙላት ያግዛል ነው ያሉት።

በደሳለኝ ቢራራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.