የህዳሴ ግድቡ ስኬት የኢትዮጵያን የመደራደር አቅም ይጨምረዋል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ላይ የተመዘገበው ስኬት የኢትዮጵያን የመደራደር አቅም ይጨምረዋል አሉ የታሪክ ባለሙያው ደረጄ ተክሌ፡፡
ከፋና ፖድካስት ጋር ቆይታ ያደረጉት አቶ ደረጄ ተክሌ እንዳሉት÷ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በርካታ ጉልበት እና ሀብት ፈጅቶ የተጠናቀቀ ነው።
የግድቡ ግንባታ ሂደት እና ስኬት የአይቻልም መንፈስን የሰበረ ነው ብለዋል፡፡
ግድቡ ሲጀመር ከሀገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ አንፃር ይጠናቀቃል ተብሎ አይጠበቅም ነበር ያሉት ባለሙያው÷ ነገር ግን ግድቡ ውሃ መያዝ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያን እድገት የማይፈልጉ ሀይሎች ግድቡ እንዳይጠናቀቅ ጫና ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በተለይም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ግድቡን ከዲፕሎማሲ ጫና አልፎ በሽብር እና በተለያዩ ኃይሎች ለማስቆም ጥረት ሲያደርጉ ነበር ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ የህዳሴ ግድቡ ውሃ መያዝ ከጀመረ ወዲህ ከኢትዮጵያ አልፎ የተፋሰሱ ሀገራት የግድቡ ደህንነት የነሱ ደህንነት መሆኑን ተረድተዋል ነው ያሉት።
የግድቡ መጠናቀቅ የኢትዮጵያን የመደራደር አቅም ከፍ አድርጎታል ያሉት ባለሙያው÷ በህዳሴ ግድቡ ላይ ቅሬታ የሚያነሱ ኃይሎችን ከሀይል አማራጭ ይልቅ ወደ አስገዳጅ ዲፕሎማሲያው ድርድር ያመጣቸዋል ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ መሆኑን በመጠቀስ ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የዓባይን ወንዝ ለመጠቀም እንደምትፈልግ ስትገልፅ መቆየቷን አውስተዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ