Fana: At a Speed of Life!

የጉግል ኩባንያ በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ቅጣት ተጣለበት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአውሮፓ ህብረት የጉግል ኩባንያ የማስታወቂያ የበላይነቱን ያለአግባብ ተጠቅሟል በሚል የ2 ነጥብ 95 ቢሊየን ዩሮ ቅጣት ጥሎበታል።

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ጉግል ኩባንያ የማስታውቂያ ህግን በመጣስ የራሱን ምርቶች በበይነ መረብ ብቻ በበላይነት በማስተዋወቅ ሌሎች ተፎካካሪ የማስታወቂያ ድርጅቶችን ጎድቷል ብሏል፡፡

ጉግል ኩባንያ በበኩሉ የተላለፈበት ውሳኔ ስህተት መሆኑን በመጥቀስ ይግባኝ እንደሚጠይቅ አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ተፎካካሪ ድርጅቶች ለማስታወቂያ ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረጉና ገቢያቸው መቀነሱን በመጥቀስ፤ የጉግል ድርጊት ደንበኞች ለአገልግሎት ከፍተኛ ገንዘብ እንዲያወጡ ምክንያት ሆኗል ነው ያለው፡፡

የጉግል ኩባንያ ዓለም አቀፍ የአስተዳደር ጉዳዮች ኃላፊ ሊ አኔ ሙልሆላንድ ቅጣቱ አግባብ አለመሆኑን በማንሳት፤ በአውሮፓ የሚገኙ በርካታ ተቋማትን ሊጎዳ የሚችል እንደሆነ ተናግረዋል።

ኩባንያው ውድድርን በሚጎዳ መልኩ ምንም አይነት የአገልግሎት አቅርቦት ችግር አለመፍጠሩን ጠቅሰው፤ በአገልግሎት ከመቼውም ጊዜ በላይ አማራጭ አብዝቷል ብለዋል።

ጉግል የራሱን ቴክኖሎጂ ለራሱ ጥቅም በማዋል ሌሎች ተፎካካሪዎቹን ጎድቷል ያለው የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን፤ ኩባንያው ከመሰል ድርጊቱ እንዲታቀብ እና የተጣለበትን የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ትዕዛዝ መስጠቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.