Fana: At a Speed of Life!

“ብዝኃነት የኢትዮጵያ ጌጥ እና ዐቅም ነው”

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብዝኃነት የኢትዮጵያ ጌጥ እና ዐቅም ነው አለ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡

አገልግሎቱ የኅብር ቀንን አስመልክቶ ያስተላለፈው መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ኢትዮጵያ በሕዝቦቿ ብዝኃ ማንነት ደምቃ፣ ፀንታና ታፍራ የኖረች፣ ብዝኃ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት የሆነች ድንቅ ሀገር ናት፡፡ ብዝኃነታችን የጥንካሬያችን፣ የሥልጣኔያችን፣ የአይበገሬነታችን፣ የክብራችን፣ የነፃነታችን እና የአልሸነፍ ባይነታችን ምሥጢር ነው፡፡

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ ጥንታዊ ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ቦታዎች እና የኪነ ሕንጻ ሀብቶቻችን የብዝኃነታችን ውጤቶች ናቸው፡፡ የአክሱም ሐውልቶች፣ የጢያ ትክል ድንጋዮች፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የለጋ ኦዳ ዋሻ ሥዕሎች፣ የጎንደር አብያተ መንግሥታት እና የሐረር ጀጎል ግንብ ኪነ ሕንጻዎች የብዝኃነታችንን ውበት እና ዐቅም ማሳያዎች ናቸው፡፡

በተለያዩ ዘመናት፣ ለተለያዩ ዓላማዎች መሠራታቸዉ የሐሳብ እና የዕውቀት ብዝኃነታችንን፣ ምንም ቴክኖሎጂ ባልነበረበት ወቅት ዘመን ተሻጋሪ ተደርገዉ መሠራታቸው የብዝኃነታችንን ዐቅም እንዲያሳዩ ያደርጋቸዋል፡፡

የባህል፣ ቋንቋ እና ዕይታ ብዝኃነቶቻችንም የኢትዮጵያ ጌጥ እና ዐቅም ናቸው፡፡ በባህላዊ የእርቅ እና ሽምግልና ሥርዐቶቻችን የአብሮነት እሴትን ገንብተናል፤ በሥነ ቃሎቻችንና ተረቶቻችን ኢትዮጵያችንን በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ቀርጸናል፡፡ ኢትዮጵያ በየባህሉ፣ በየቋንቋዉ፣ በየማኅበረሰቡ ታሪክ እና ትርክት የጸናች የወል እውነታችን የኾነችዉ በብዝኃነታችን እሴቶች ነው፡፡

የአለባበስ፣ የአመጋገብ፣ የኀዘንና ደስታ አገላለጽ ብዝኃነቶቻችን ኢትዮጵያን ማስጌጫ ቀለሞቻችን ናቸው፤ ለዚህም ነው በኅብር ቀን ልናጎላቸው የወደድነው፡፡ ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ልዩ ወር በኾነችዉ ጳጒሜን 2ኛ ቀን የኅብር ቀንን ብዝኃነት የኢትዮጵያ ጌጥ በሚል መሪ መልእክት ማክበራችን፡፡

ብዝኃነታችን ጌጣችን ብቻ አይደለም፤ ዐቅማችንም እንጅ፡፡ ኢትዮጵያውን በጋራ ሞክረን ያላሳካነው የለም፡፡ እንደ ዓድዋ ያለ በዓለም የነጻነት ትግል ቀንዲል የኾነ ድል ስናሳካ ብዝኃነታችን ዐቅማችን ነበር፡፡ አንደኛችን የተዋጣልን ቀስተኞች ነበርን፤ አንደኛችን የተዋጣልን ፈረሰኞችና ጦረኞች ነበርን፤ ሌላኛችን በባህላዊ መንገድ ሐኪሞች ነበርን፤ ሌላኛችን የተዋጣልን ጀግና ቀራጪ ከያኒ ነበርን፡፡

የእያንዳንዳችን ብዝኃ ዕውቀት ዓድዋን ወለደ፡፡ በዚህም ዘመን ብዝኃነታችን ዐቅማችን ለመኾኑ ዳግማዊ ዓድዋችን ኅዳሴ ምስክር ነው፡፡ ገንዘባችንን፣ ላባችንን፣ ጉልበትና ዕውቀታችንን ደምረን፣ ዓለማቀፍ ጫናዎችን ተቋቁመን ኅዳሴን ያሳካነው ብዝኃነታችን በፈጠረልን ዐቅም ነው፡፡ በአረንጓዴ ዐሻራ በየዓመቱ የራሳችንን ክብረ ወሰን እያሻሻልን ዓለምን የምናስደምመው ብዝኃነታችን በፈጠረልን ዐቅም ነው፡፡

ለዚህም ነው ብዝኃነት የኢትዮጵያ ጌጥ የምንለው፡፡ ለዚህ ነው ጳጉሜን 2ን የኅብር ቀን ብለን የምናከብረው፡፡ ኢትዮጵያ በብዝኃነቷ እያጌጠች፤ በብዝኃነቷ ዐቅም እያደገች፤ ዐዲሲቷ የተስፋ ዓድማስ ትኾናለች፡፡ የማንሰራራት ዘመኗም በብዝኃነቷ ያጌጣል፡፡

ጳጒሜን 2 ቀን 2017 ዓ.ም

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.