Fana: At a Speed of Life!

በካናዳ የምክክር መድረክ የተሳተፉ ወኪሎች አጀንዳቸውን ለኮሚሽኑ አስረከቡ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በካናዳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ ለማሰባሰብና በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ ወኪሎችን ለመምረጥ በቶሮንቶ ያካሄደው መድረክ በስኬት ተጠናቅቋል፡፡

በመድረኩ በሀገር ውስጥ በትግል ላይ የሚገኙ አካላትን እንወክላለን ያሉ ተሳታፊዎች ጭምር ጥያቄዎቻቸውን በግልጽ አቅርበዋል፡፡

አንዳንድ ተሳታፊዎች በተቃውሞ ስሜት ሃሳብና አስተያየታቸውን በነፃነት ያቀረቡ ሲሆን÷ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ተሳታፊዎች ተቃውሞ ቢኖራቸውም በውይይቱ እንዲቀጥሉ በማድረግ የምክክር ሜዳን ሰፊነት አሳይተዋል፡፡

በተቃውሞ ድምፀት ለተነሱ ጥያቄዎችም በትዕግስትና በብስለት ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ከሁሉም ጎራ የመጡ ኢትዮጵያዊያን በጋራ እንዲመካከሩ አስችለዋል፡፡

በኮሚሽሮቹ ምላሽና ማብራሪያ መግባባት ላይ የደረሱት ተሳታፊዎቹ በቡድን በቡድን በመሆን ሀገራዊ ፋይዳቸው የጎላ አጀንዳዎችን አደራጅተው እና በሀገራዊ ጉባዔው የሚሳተፉ ወኪሎችን መርጠው ለኮሚሽኑ አስረክበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሒሩት ገብረስላሴ በካናዳ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ላደረጉት ተሳትፎ ማመስገናቸውን ኮሚሽኑ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ ማንኛውንም አይነት ሀሳብ እና ጥያቄ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን የገለፁት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ÷ በሆደ ሰፊነት በመመካከር፣ ለሀገራችን ችግሮች ፈውስ እናምጣ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.