የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለፊፋ ቅሬታ አቀረበ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ እና ግብፅ ባለፈው አርብ ምሽት ካደረጉት ጨዋታ ጋር በተገናኘ ለፊፋ ቅሬታ አቅርቧል፡፡
ፌደሬሽኑ በጨዋታው ላይ የተፈፀመውን የስነምግባር ጉድለት ተከትሎ ነው ለዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ቅሬታውን ያቀረበው፡፡
ለፊፋ ቅሬታ የቀረበው በሁለት ዋና ዋና የስነምግባር ጥሰቶች ላይ ሲሆን፥ አንደኛው ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር ሲዘመር የግብፅ ብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች የፈጸሙትን ተገቢ ያልሆነ ድርጊት የተመለከተ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የግብፅ ብሔራዊ ቡድን የፍፁም ቅጣት ምት ባገኘበት ወቅት የፈርኦኖቹ ደጋፊዎች የዋልያዎቹ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑራ ዓይን ላይ መብራት አብርተዋል ሲል ክስ ማቅረቡን ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡