የክልሉን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የፀጥታ መዋቅሩ ይጠናከራል – ወ/ሮ ዓለሚቱ ኡሞድ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጋምቤላ ክልል ያለውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የፀጥታ መዋቅሩን የማጠናከሩ ተግባር ይቀጥላል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ።
ወ/ሮ ዓለሚቱ በክልሉ የቦንጋ ፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም የሰለጠኑ የአድማ ብተና የፖሊስ አባላት ምረቃ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ የተጀመረውን የልማትና የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ መንግስት በሁሉም መስኮች ያልተቆጠበ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ባለፈ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩ በማድረግ ረገድ ስኬታማ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ተመራቂ የአድማ ብተና የፖሊስ አባላት በስልጠናው ያገኙትን ክህሎት ወደ ተግባር በመለወጥ የክልሉን ህዝብ ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ ረገድ የተጣለባቸውን ኃላፊት እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ማህበር ኮር በበኩላቸው÷ በክልሉ ያለውን አስተማማኝ ሰላም ለማጽናት የፀጥታ መዋቅሩን የማጠናከርና ከሕብረተሰቡ ጋር በቅንጅት የመስራት ተግባር በመከናወን ላይ እንደሆነ ማንሳታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል ገልጿል።