Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የደመቀችበት የሄልሲንኪ የዓለም ሻምፒዮና ሲታወስ…

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የ2025 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ከእኩለ ሌሊት በኋላ በጃፓን ቶኪዮ ጅማሮውን ያደርጋል፡፡

በርካታ አትሌቶችም የኢትዮጵያ ስም እንዲናኝ፣ ሰንደቋም በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያስቻሉ ቀደምት አትሌቶችን ፈለግ ተከትለው በሻምፒዮናው ላይ ለግል ስኬታቸው ብሎም ለሀገራቸው ክብር ይወዳደራሉ፡፡

ለአሸናፊነት ቅድመ ግምት የተሰጣቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ወደ ሩቅ ምስራቋ ጃፓን ያቀኑ ሲሆን በተለያዩ ርቀቶች ሀገራችንን ይወክላሉ፡፡

የዓለም ሻምፒዮና ሲነሳ በተለይም በሴቶች 5ሺህ ሜትር አራት ኢትዮጵያውያን ከ1 እስከ 4 ተከታትለው የገቡበት የ2005ቱ የሄልሲንኪ ሻምፒዮና አይረሳም፡፡

በፈረንጆቹ 2005 በፊንላንድ ሄልሲንኪ በተካሄደው ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በ15 ወንዶችና በ13 ሴት አትሌቶች በተሳተፈችባቸው 10 ርቀቶች ስምንት ሜዳልያዎችን አግኝታለች፡፡

በሻምፒዮናው ከተገኙ 3ቱ የወርቅ ሜዳልያዎች ውስጥ ሁለቱን ጥሩነሽ ዲባባ በ10ሺህ እና 5ሺህ ሜትር ያስገኘች ሲሆን፥ ሌላኛውን የወርቅ ሜዳልያ ቀነኒሳ በቀለ በወንዶች 10 ሺህ ሜትር አስገኝቷል፡፡

በተለይም ኢትዮጵያውያኑ ከ1 እስከ 4 ተከታትለው በመግባት አረንጓዴውን ጎርፍ ለዓለም ያስመለከቱበት የሴቶች 5ሺህ ሜትር በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሁሌም የሚታወስ ነው፡፡

በወቅቱ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የውድድሩን ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር ርቀቱን በቀዳሚነት ስታጠናቅቅ፥ መሰረት ደፋር፣ እጅጋየሁ ዲባባ እና መሰለች መልካሙ ከ2 እስከ 4ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ በውድድሩ ደምቀዋል፡፡

ይህም በዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በርቀቱ የአንድ ሀገር አትሌቶች ከ1 እስከ 4 ያለውን ደረጃ ይዘው በበላይነት ያጠናቀቁበት የመጀመሪያውና ብቸኛው ሁነት ሆኖ በታሪክ ሰፍሮ ይገኛል፡፡

ሌላኛው የኢትዮጵያና የሄልሲንኪውን ሻምፒዮና ቁርኝት ያጠበቀው ውድድር ደግሞ ጥሩነሽ ዲባባ ብርሃኔ አደሬንና እህቷን እጅጋየሁ ዲባባን አስከትላ የገባችበት የሴቶች 10ሺህ ሜትር ነው፡፡

በወንዶች 10ሺህ ሜትር ቀነኒሳ በቀለ በበላይነት ያጠናቀቀ ሲሆን፥ የወቅቱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ስለሺ ስህን በበኩሉ ለኢትዮጵያ የብር ሜዳልያ አስገኝቷል፡፡

ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ በጃፓን ቶኪዮ በሚደረገው የዘንድሮው የዓለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች መሰል ደማቅ ታሪክ እንደሚጽፉ ይጠበቃል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.