Fana: At a Speed of Life!

በአዲሱ የውድድር ዘመን የሪያል ማድሪድ ጅማሮ …

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሪያል ማድሪድ በ2024/25 የውድድር ዘመን ባለፉት ዓመታት ሲያደርግ እንደነበረው በዋንጫዎች የታጀበ ጊዜ ማሳለፍ አልቻለም ነበር።

በውድድር ዘመኑ በምንጊዜም ተቀናቃኙ ባርሴሎና ላሊጋውን ጨምሮ ሌሎች የውስጥ ውድድር ዋንጫዎችን ተነጥቋል።

ሪያል ማድሪድ የ2024/25 የውድድር ዓመት ከመጀመሩ አስቀድሞ ካለው የስብስብ ጥራት አንጻር በዋንጫ የታጀበ ጊዜ ያሳልፋል ተብሎ ቢጠበቅም አልተሳካለትም።

ሎስብላንኮቹ የላሊጋውን ዋንጫ ከማጣታቸው ባለፈ የእነሱ ውድድር እንደሆነ ከሚነገርለት የአውሮፓ ሻምፒየንስ ዋንጫ መድረክ በሩብ ፍጻሜው ነበር የተሰናበቱት።

አሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ ኪሊያን ምባፔ፣ ቪኒሸስ ጁኒየር፣ ሮድሪጎ፣ ጁድ ቤሊንግሀም፣ ፌድሪኮ ቫልቬርዴ እንዲሁም አንጋፋዉ ተጫዋች ሉካ ሞድሪች እና ሌሎች ከዋክብቶችን ይዘው ፈታኝ የውድድር ጊዜን ነበር ያሳለፉት።

ካርሎ አንቸሎቲን ተክቶ ሳንቲያጎ ቤርባው የደረሰው የቀድሞ ተጫዋቻቸው የአሁኑ የቡድኑ አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ በአዲሱ የውድድር ዓመት ጥሩ ጅማሮ ላይ ይገኛል።

ዣቪ በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት አሌክሳንደር አርኖልድ፣ ዲን ሁይሰን፣ ፍራንኮ ማስታንቱኖ እና አልቫሮ ካሬራስ የመሳሰሉ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ በመቀላቀል ቡድኑን የማጠናከር ስራ በመስራት አዲሱን የውድድር ዘመን ጀምሯል።

ሪያል ማድሪድ በ2025/26 የውድድር ዘመን በዣቪ አሎንሶ እየተመራ በላሊጋው እስካሁን ያደረጋቸውን ስድስት ጨዋታዎች በሙሉ በማሸነፍ ላሊጋውን እየመራ ይገኛል።

ስድስቱንም የላሊጋ ጨዋታዎች ያሸነፈው ሪያል ማድሪድ ተጋጣሚዎቹ ላይ 14 ጎሎችን ሲያስቆጥር የተቆጠረበት 3 ጎል ብቻ ነው።

አምና ማድሪድ ወጥ ብቃት ለማሳየት ቢቸገርም ፈረንሳዊው ኮከብ ኪሊያን ምባፔ ግን በግሉ ጥሩ ጊዜን ማሳለፉ ይታወሳል።

ካለፈው የውድድር ዘመን ይበልጥ ጠንክሮ የመጣ የሚመስለው ኪሊያን ምባፔ በላሊጋው ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች 7 ጎሎችን አስቆጥሮ አንድ ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል።

ሌላው ባለፈው የውድድር ዓመት አቋሙ እንደወረደ ሲነገር የነበረው ቪኒሸስ ጁኒየር በላሊጋው ባደረጋቸው 6 ጨዋታዎች 3 ጎል አስቆጥሮ 3 ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

በ2024/25 የውድድር ዘመን የተጠበቀውን ያህል ውጤታማ ያልሆነው እና በተቀናቃኙ ባርሴሎና የበላይነት የተወሰደበት ሪያል ማድሪድ በዚህኛው የውድድር ዓመት እስካሁን ያደረጋቸውን ሁሉንም ጨዋታዎች በመርታት አጀማመሩን አሳምሯል።

አስልጣኝ ዣቪ አሎንሶ ቡድናቸው እስካሁን ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በሙሉ ቢያሸንፍም ውህደት ላይ ቀሪ የቤት ስራ እንዳለበት ተናግረዋል።

ጥሩ የውድድር ዘመን ጅማሮ ላይ የሚገኘው ሪያል ማድሪድ የፊታችን ቅዳሜ ደካማ የውድድር ዓመት ጅማሮ እያሳየ ከሚገኘው ከከተማ ተቀናቃኙ አትሌቲኮ ማድሪድ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ይጠበቃል።

ባለፈው የውድድር ዘመን በዋንጫ የታጀበ ዓመት ማሳለፍ ያልቻለዉ ሪያል ማድሪድ በዚህኛው የውድድር ዘመን ስኬታማ ጊዜ ለማሳለፍ አሸናፊነቱን ማስቀጠል ይጠበቅበታል።

በተለይም በ2024/25 የውድድር ዓመት በሁሉም ውድድሮች በባርሴሎና የተወሰደበትን የበላይነት የማስመለስ ስራ ትልቁ የሎስብላንኮቹ የቤት ስራ ነው።

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.