ቢሾፍቱ የሀርሰዴ ኢሬቻ በዓልን ለማክበር ዝግጅት አድርጋ እንግዶችን ተቀብላለች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አለማየሁ አሠፋ የሀርሰዴ ኢሬቻ በዓልን ለማክበር አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገን እንግዶችን ተቀብለናል አሉ።
የቢሾፍቱ ከተማ ዘንድሮ በኮሪደር ልማት ተውባ እንግዶቿን በደማቅ ሁኔታ ተቀብላለች።
የዘንድሮ የኢሬቻ በዓል በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ታቅደው ተግባራዊ እየተደረጉ ባሉበት ጊዜ መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ያሉት ከንቲባው፤ የገዳ ስርዓት መገለጫ የሆነው የኢሬቻ በዓል አብሮነት፣ ወንድማማችነት እና አንድነት የሚንጸባረቅበት እንደሆነ ተናግረዋል።
የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጎ እንግዶችን በኢትዮጵያዊነት የእንግዳ አቀባበል ስርዓት መቀበሉን ገልጸዋል።
ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ተስማሚ እና ለበዓሉ ተሣታፊዎችም የተመቸች በማድረግ ረገድ በርካታ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
ከተማዋን ግንባር ቀደም የቱሪዝም መዳረሻነቷን ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።
የበዓሉ ታዳሚዎች ምንም ዓይነት የአቅርቦት ችግር እንዳይገጥማቸው ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በቅንጅት መሰራቱንም ጠቅሰዋል።
በዓሉ በድምቀት ተከብሮ እንዲጠናቀቅ በዋና ዋና ጎዳናዎች እና በዓሉ በሚከበርበት ሥፍራ በዘመናዊ የደኅንነት ካሜራዎች የታገዘ የጸጥታ ሥራ እንደሚጠናከር መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ወደ ቢሾፍቱ ለመጡ እንግዶች መልካም አቀባበል ላደረጉ የከተማዋ ነዋሪዎች ምስጋናም አቅርበዋል።