ሩበን አሞሪም በ3 ዓመታት ውስጥ ምርጥ አሰልጣኝነቱን ማሳየት አለበት – ሰር ጂም ራትክሊፍ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማንቼስተር ዩናይትድ ባለድርሻ የሆኑት ሰር ጂም ራትክሊፍ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ውስጥ ምርጥ አሰልጣኝነቱን ማሳየት አለበት አሉ፡፡
ሰር ጂም ራትክሊፍ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም በማንቼስተር ዩናይትድ ቤት በቂ ጊዜ እንደሚሰጠው ገልጸው፤ ታላቅ አሰልጣኝ መሆኑን ለማረጋገጥ ሶስት ዓመታት ያስፈልጉታል ብለዋል፡፡
ሩበን አሞሪም ከፖርቹጋል ወደ ኦልድትራፎርድ ከመጣ በኋላ በቀያይ ሰይጣኖቹ ቤት ጥሩ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ አይደለም፡፡
ዩናይትድ ባለፈው የውድድር ዘመን በፕሪሚየር ሊጉ 15ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን ከፈረንጆቹ 1973/74 የውድድር ዘመን በኋላ በክለቡ ታሪክ መጥፎ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
በክረምቱ የተጫዋች የዝውውር መስኮት ከ200 ሚሊየን ፓውንድ በላይ ወጪ ያደረገው ዩናይትድ ጥሩ ጅማሮ ላይ አይገኝም፡፡
ራትክሊፍ እንደገለጹት፤ አሞሪም የራሱን ዋጋ ለማረጋገጥ ረዘም ያለ ጊዜ ያስፈልገዋል።
ሩበን በሶስት ዓመታት ውስጥ ታላቅ አሰልጣኝ መሆኑን ማሳየት አለበት ሲሉ በአፅንኦት መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በዚህ የውድድር ዓመት ዩናይትድ በሊጉ ካደረጋቸው 7 ጨዋታዎች ሶስት አሸንፎ፣ ሶስት ተሸንፎ እንዲሁም በአንዱ አቻ ተለያይቶ 10 ነጥብ በመያዝ በሊጉ ሰንጠረዥ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ማንቼስተር ዩናይትድ በሜዳ ላይ ውጤት ደካማ ቢሆንም ትርፋማ ክለብ መሆኑ ይታወቃል፡፡