የባሕር በር ጥያቄውን ለማስመለስ ዜጎችን ያሳተፈ ዲፕሎማሲ ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባሕር በር ጥያቄውን ለማስመለስ ዜጎችን ያሳተፈ ዲፕሎማሲ ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል።
የዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እንዳለ ንጉሴ ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲ ታሪክ ያላት፣ የአፍሪካ ሕብረትን የመሰረተች እና የአፍሪካ ሀገራት ነጻ እንዲወጡ መንገድ የጠረገች መሆኗን አንስተው÷ የባሕር በር ማጣቷ ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር ፍጹም ስህተት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ እድገት ለጎረቤት ሀገራት በረከት እንደሆነና ችግሯ ደግሞ ተመሳሳይ ሕዝብ፣ ቋንቋ እና ባህል እንደመጋራታችን ለጎረቤት ሀገራትም የሚተርፍ መሆኑን ገልጸው÷ የባሕር በር ጥያቄውን መደገፍ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የዲፕሎማሲ ዋናው ማዕከል ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ እንደሆነ የገለጹት መምህር እንዳለ÷ ከለውጡ ወዲህ ኢትዮጵያ ማሻሻያ ካደረገችባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ዲፕሎማሲው ነው ብለዋል።
የባሕር በር ጥያቄውን ለማስመለስ ዜጎችን ያሳተፈ ዲፕሎማሲ ላይ በትኩረት መስራት አስፈላጊ መሆኑንም አመልክተዋል።
ወደ የትኛውም ወገን ባለማድላት ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ በሚቻልበት መልኩ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲውን መጠቀም እንደሚገባም አጽንዖት ሰጥተዋል።
ዲፕሎማሲ የመንግሥታት ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ዜጎችን ያሳተፈ እና ዜጎች በሄዱበት ቦታ የሀገራቸው አምባሳደር እንዲሆኑ ማድረግን የሚፈልግ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ለሀገራት እድገት የባሕር በር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አብራርተዋል።
በብርሃኑ አበራ
መምህር እንዳለ ንጉሴ ከፋና ፖድካስት ጋር ያደረጉትን ቆይታ ለመከታተል ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ👇
https://www.youtube.com/watch?v=revGFzM73po