Fana: At a Speed of Life!

የስማርት ስልክ አጠቃቀም ሰዎችን በማራራቅ ላይ የሚገኝ ወረርሽኝ ሆኗል – የዌልስ ልዕልት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከመጠን ያለፈ የስማርት ስልክ አጠቃቀም ሰዎችን በማራራቅ የቤተሰብ ህይወትን በማወክ ላይ የሚገኝ ወረርሽኝ ሆኗል አሉ የዌልስ ልዕልት ኬት ካትሪን፡፡

ልዕልቷ እንደሚሉት፥ እነዚህ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች ሰዎችን ያቀራርባሉ ተብሎ ቢታሰብም፤ ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒው ማህበራዊ ግንኙነትን ክፉኛ እየጎዱት ይገኛሉ፡፡

ልዕልት ኬት ካትሪን ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ኮሌጅ ፕሮፌሰር ሮበርት ዋልዲንገር ጋር በመሆን ባስነበቡት ጽሁፍ፥ ስማርት ስልኮች ትኩረታችንን በማሳጣት ከቤተሰብ ጋር ልናሳልፋቸው የሚገቡንን ጊዜያት እያባከኑ ነው ብለዋል፡፡

ጠንካራ የቤተሰብና የሰው ለሰው ግንኙነት ለአዕምሮም ሆነ ለአካል ጤንነት መሰረት መሆኑን ጥናቶችን ዋቢ አድርገው ያስረዱት ልዕልቷ፥ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ይሄንን ለሰው ልጆች መሰረታዊ የሆነውን ጸጋ እያሳጣ መሆኑን ነው የሚገልጹት፡፡

በአሁኑ ወቅት በማኅበረሰብ ውስጥ ብዙ ብቸኛ የሆኑና የተገለሉ ሰዎችን ማየት እየተለመደ መምጣቱን ጠቅሰው፥ ይህም ለአዕምሯዊ እና አካላዊ ጤና መቃወስ ምክንያት ሆኗል ነው ያሉት፡፡

በዚህ በተዋከበ ዓለም ውስጥ ሰዎች በስማርት ስልኮችና በኮምፒዩተሮች ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ በመቀነስ የጋራ የቤተሰብ ጊዜን ማሳለፍ፣ እርስ በእርስ መገናኘትና ሐሳብ መለዋወጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ዓለም በቴክኖሎጂ ሽብር ውስጥ ትገኛለች ሲሉም ነው ልዕልት ኬት ካትሪን የሚገልጹት፡፡

ባለቤታቸው ልዑል ዊሊያም በቅርቡ ከአፕል ቲቪ ሾው ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ሦስቱም ልጆቻቸው ስማርት ስልኮች እንዳይጠቀሙ መከልከላቸውን ተናግረዋል፡፡

በአቤል ነዋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.