የዲጂታል ዘርፉ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽዖ እያበረከተ ነው – አቶ አህመድ ሺዴ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዲጂታል ዘርፉ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽዖ እያበረከተ ነው አሉ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተሳተፉበት 24ኛው የኮሜሳ መሪዎች ጉባኤ “ዲጂታላይዜሽንን ለቀጣናዊ የእሴት ሰንሰለት መጎልበት በመጠቀም ለዘላቂ እና አካታች እድገት ማዋል” በሚል መሪ ሐሳብ ተካሂዷል።
የመሪዎች ጉባኤውን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የዲጂታል መሰረተ ልማትን በማልማት ረገድ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን መግለፃቸውን አንስተዋል።
የዲጂታል ክህሎትን በማሳደግ ከፍተኛ ስራ የተሰራበትና በዚህም ትልቅ ውጤት የመጣበት ሀገር መሆኑን ጠቅሰው÷ ባለፉት ሰባት ዓመታት ለኢኮኖሚ ሪፎርም ስራ ማዕከል የነበረውን የዕድገት ምንጮችንን ማስፋት እንደሆነና የግሉን ዘርፍ ተዋናይ በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በተለይም የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያሳልጡ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ዋነኛ የሪፎርሙ ተልዕኮ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም አንዱና ዋነኛው ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ የነበረው የዲጂታላይዜሽን ልማት እንደሆነና ራሱን ችሎ ሰፊ ስትራቴጂ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
የዲጂታል ዘርፉ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽዖ እያበረከተ ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ በዚህም ቀጣናውን በማስተሳሰር ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወት ነው ብለዋል።
በአድማሱ አራጋው