Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የዲጂታል ህልሟን ወደ ተግባር የምትቀይርበትን ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ እየተገበረች ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የዲጂታል ህልሟን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችላትን ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ እየተገበረች ትገኛለች አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ24ኛው የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በዓለም ላይ በፍጥነት እየተለወጠ የመጣው ቴክኖሎጂ የሀገራትን እድገት፣ የማህበረሰብ ትስስር እና የጋራ ብልጽግናን የማረጋገጥ ጉዞ እየወሰነ ይገኛል ብለዋል።
አፍሪካ አሁን ቆማ የምታይበት እና የምትጠብቅበት ጊዜ አለመሆኑን ጠቅሰው÷ ያለውን በርካታ የህዝብ ቁጥር፣ የፈጠራ አቅም እና የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም የበለጸገች እና መጻኢ ጊዜዋ ፍትሃዊ እንዲሆን ለማድረግ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ለዚህም ጥረቶቻችንን በማስተሳሰር እና የጋራ ጥቅማችንን ባስጠበቀ መልኩ ርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
እንደ ኮሜሳ ያሉ ቀጣናዊ ተቋማት ያላቸው ፋይዳ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትልቅ መሆኑን ጠቅሰው÷ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የአፍሪካ ኢኮኖሚን ታሪክ ዳግም ለመጻፍ ልዩ እድል ይዞ መምጣቱንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በ100ዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ማድረጓን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ከ25 ሚሊየን በላይ ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት መሆን መቻላቸውን ተናግረዋል።
በ2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ ስርዓት ምህዳር በቢሊየኖች የሚቆጠር የገንዘብ ግብይት መፈጸሙንና በብሄራዊ የኮዲንግ ፕሮግራም ወጣት ኢትዮጵያውያን ኢኖቬተር መሆን የሚያስችላቸውን ስልጠና በመውሰድ የብቃት ማረጋገጫ ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ተሞክሮዎች አፍሪካ በክህሎት እና ዲጂታል ፋውንዴሽን ላይ መዋዕለ ነዋይ ካፈሰሰች በዓለም ደረጃ በራሷ መመዘኛዎች ተወዳዳሪ መሆን እንድምትችል ማሳያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የዲጂታል ራዕይን እውን ለማድረግ፣ የዲጂታል አቅምን ወደ ቀጣናዊ ኃይል ለመቀየር እና አሳታፊነትን ወደ ጋራ ብልጽግና ለማሸጋገር ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን አመላክተዋል።
መጪው ጊዜ የሚሸልመው ዛሬ የተገነባውን በመሆኑ ለዚህም በጋራ እንስራ እንትጋ ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.