የአፍሪካ ሀገራት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች…
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጋራ ለሚያስተናግዱት የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የአፍሪካ ሀገራት ማጣሪያ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ ይደረጋሉ፡፡
በማጣሪያው ምድቦቻቸውን እየመሩ የሚገኙት አራቱ የሰሜን አፍሪካ ሀገራት ግብጽ፣ ሞሮኮ፣ ቱኒዚያ እና አልጄሪያ ከወዲሁ የዓለም ዋንጫ ትኬታቸውን ቆርጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ምድብ -1 በ23 ነጥቦች እየመራች የምትገኘው ግብጽ በነገው ዕለት ከጊኒ ቢሳው ጋር ከምታደርገው የምድብ የመጨረሻ ጨዋታ አስቀድማ ማለፏን አረጋግጣለች፡፡
በምድብ-5 ሁሉንም ነጥብ መሰብሰብ የቻለችው ሞሮኮ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዋን ሳትጠበቅ ከወዲሁ በቀጥታ የዓለም ዋንጫውን ከሚቀላቀሉት ዘጠኝ ሀገራት አንዷ መሆን ችላለች፡፡
አልጄሪያ እና ቱኒዚያ በተመሳሳይ የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ መሆናቸውን ከወዲሁ ያረጋገጡ ሀገራት ናቸው፡፡
ከየምድቦቻቸው በቀጥታ የሚያልፉ ሌሎች አምስት ብሔራዊ ቡድኖች የሚለዩባቸው የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ ይከናወናሉ፡፡
ምድብ ሁለትን እየመራች የምትገኘው የሳዲዮ ማኔ ሀገር ሴኔጋል ነገ ከሞሪታንያ ጋር የምታደርገውን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለች ሌሎች ጨዋታዎችን ሳትጠበቅ በዓለም ዋንጫው አፍሪካን የምትወክል ሌላኛዋ ሀገር ትሆናለች፡፡
ከሌሎች ምድቦች በተለየ ሁኔታ ሦስት ሀገራት ምድባቸውን በበላይነት የማጠናቀቅ እድል ይዘው በሚፎካከሩበት ምድብ ሦስት የሚደረጉ የመጨረሻ ጨዋታዎች ተጠባቂ ናቸው፡፡
ምድቡን እየመራች የምትገኘው ቤኒን ሦስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘውን ናይጄሪያ ማሸነፍ ከቻለች ለመጀመሪያ ጊዜ የመድረኩ ተሳታፊ መሆኗን ታረጋግጣለች፡፡
ናይጄሪያ ምድቡን በበላይነት በማጠናቀቅ በቀጥታ ወደ ዓለም ዋንጫው ለማለፍ ከቤኒን ጋር የምታደርገውን ጨዋታ ከማሸነፍ ባለፈ በምድብ ሁለት የምትገኘውን ደቡብ አፍሪካ ነጥብ መጣል ትጠብቃለች፡፡
ደቡብ አፍሪካ በአንጻሩ በቀጥታ የመድረኩ ተሳታፊ ለመሆን ከሩዋንዳ ጋር የምታደርገውን የመጨረሻ ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅባታል፡፡
ባፋና ባፋናዎቹ ሩዋንዳን ከማሸነፍ በተጨማሪ የቤኒንን መሸነፍ የሚጠብቁ ሲሆን፥ ቤኒን ነጥብ የምትጋራ ከሆነ በሦስት ግብ ልዩነት ማሸነፍ ወደ ዓለም ዋንጫው በቀጥታ መግባት ያስችላቸዋል፡፡
ኬፕ ቨርዴ እና ካሜሮን በተፋጠጡበት ምድብ አራት ኬፕ ቨርዴ በምድቡ ግርጌ የምትገኘውን ኢስዋቲኒ ማሸነፍ በቀጥታ የዓለም ዋንጫው ተሳታፊ ያደርጋታል፡፡
በምድቡ 2ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ካሜሮን አንጎላን ከማሸነፍ ባለፈ የኬፕ ቨርዴን መሸነፍ አልያም ነጥብ መጣል ትጠብቃለች፡፡
ምድብ ስድስትን እየመራች የምትገኘው ኮት ዲቯር ኬንያን በምታስተናግድበት የመጨረሻ ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለች ሌሎች ውጤቶችን ሳትጠብቅ በቀጥታ የዓለም ዋንጫው ተሳታፊ ትሆናለች፡፡
በፔር ኤመሪክ ኦበሚያንግ አራት ጎሎች ታግዛ ጋምቢያን 4 ለ 3 በማሸነፍ ለዓለም ዋንጫ የማለፍ እድሏን ያለመለመችው ጋቦን በቀጥታ ለማለፍ ቡሩንዲን ከማሸነፍ በተጨማሪ የኮት ዲቯርን መሸነፍ ትጠብቃለች፡፡
በምድብ ዘጠኝ 2ኛ ደረጃ ላይ ከምትገኘው ማዳጋስካር በሦስት ነጥብ እና በስምንት የግብ ልዩነት በመብለጥ ምድቡን እየመራች የምትገኘው ጋና ሌሎች ጨዋታዎችን ሳትጠብቅ በቀጥታ ለማለፍ አቻ በቂ ውጤቷ ነው፡፡
ከየምድቦቻቸው በቀጥታ ከሚያልፉ ዘጠኝ ሀገራት በተጨማሪ ምርጥ 2ኛ በመሆን ከሚያጠናቅቁ አራት ሀገራት መካከል አንዳቸው በፊፋ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች መርሐ ግብር በኩል ለዓለም ዋንጫው የመሳተፍ እድል አላቸው፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ