በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን የባህር በር ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም -ምሁራን
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ከማስጠበቅ የሚመነጭ የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳ በመሆኑ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም አሉ የዘርፉ ምሁራን፡፡
ምሁራኑ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ኢትዮጵያ በተፈፀመባት ታሪካዊ ስህተትና ኢ-ፍትሐዊ በሆነ ሁኔታ የባሕር በር አልባ እንድትሆን መደረጉን አስታውሰዋል፡፡
በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ኤዞ አመቆ (ዶ/ር) እንደሚሉት፥ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር በቅርብ ርቀት የምትገኝና የብዙ ሕዝብ ባለቤት ሀገር መሆኗ የባህር በር ከሌላቸው ሀገራት የተለየ ያደርጋታል፡፡
በዓለም የንግድ ሥርዓት በሸቀጦች እንቅስቃሴ ግዙፍ ስፍራ በሚሰጠው የቀይ ባሕር ላይ የባህር በር ማጣት በሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ኪሳራው ብዙ መሆኑን አስረድተዋል።
የባሕር በር ባለመኖሩ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ የገቢና ወጪ የንግድ ሥርዓት ለከፍተኛ ወጪ እንድትጋለጥ ማድረጉንም ነው ምሁሩ የተናገሩት፡፡
በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ የታሪክና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ሰይድ አህመድ (ዶ/ር) በተመሳሳይ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታጣ መደረጉ በገቢና ወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትና በዜጎች ኑሮ ላይ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረትና በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት ሥርዓት ውስጥ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የባሕር በርና የወደብ አገልግሎት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ነው ምሁራኑ የሚገልጹት፡፡
አሁን በዓለም ላይ በኢኮኖሚያቸው ቁንጮ የተቀመጡ ሀገራት በራቸውን ክፍት አድርገው በንግድ ስርዓቱ የሚሳተፉ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሰፊ ቆዳና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባለቤት እንዲሁም ለቀይ ባህር በቅርብ ርቀት የምትገኝ እንደመሆኗ የባሕር በር የማግኘት ፍትሐዊ ጥያቄዋ የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳና የህልውና ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
የባሕር በር መሻቷ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና ተጠቃሚነትን ከማሳለጥ የሚመነጭና ቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነትና ዓለም አቀፍ መርህን የተከተለ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ጥያቄ ማቅረቧ ለዓለም ገበያ በር መክፈት ነው ያሉት ኤዞ አመቆ (ዶ/ር)፥ አባል ስትሆን ተወዳዳሪና የተሳለጠ ንግድ እንዲሁም በነፃነት ምርቶችን የምታስገባበትና የምታስወጣበት የባህር በር ሊኖራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ወደብ ማግኘት የኢኮኖሚ የበላይነትና ነጻነት ለማግኘት ያስችላል የሚሉት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ፥ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን መንግስት የባህር በር ለማግኘት እየሄደበት ያለው ሂደት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በኢብራሂም ባዲ