በኦሮሚያ ክልል በትምህርቱ ዘርፍ የተመዘገበው ውጤት አርዓያ የሚሆን ነው – የትምህርት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል መንግስት ትምህርትን ቀዳሚው አጀንዳ በማድረግ ያስመዘገበው ውጤት ለሌሎች አርዓያ የሚሆን ነው አሉ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ።
የኦሮሚያ ክልል የትምህርት ጉባዔ “ትምህርት ለሰው ሃብት ልማት” በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ሚኒስትር ዴኤታዋ ባስተላለፉት መልዕክት÷ የክልሉ መንግሥት ትምህርትን አጀንዳ አድርጎ በመስራት ያስመዘገበው ውጤት የሚያስመሰግን እና ለሌሎች ክልሎችም አርዓያ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።
ትምህርት የግለሰብን ኑሮ በማሻሻል ለሀገር ብልጽግና መሰረት እንደሚሆን ገልጸው÷ በየደረጃው የሚሰጥ ትምህርት ዘመኑን የዋጀ ክህሎት ያለው፣ ከቴክኖሎጂ ጋር የተስማማ፣ ችግር ፈቺ እና መፍትሄ አመላካች መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
የትምህርት ፖሊሲ በማዘጋጀት እና አዋጅ በመዘርጋት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የትምህርት ስርዓቱን የተሻለ ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል።
በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በመንግሥትና በሕዝብ ተሳትፎ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች በመገንባት፣ ግብዓቶች በማሟላትና ደረጃቸውን በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ውጤት መመዝገቡን አብራርተዋል።
የቅድመ መደበኛ ትምህርትን ለማስፋፋት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው÷ ክልሉ ሕብረተሰቡን በማስተባበር በሺዎች የሚቆጠሩ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች መገንባቱ ለሌሎች ክልሎች አርዓያ ይሆናል ነው ያሉት።
በተጨማሪም ባለፉት ሁለት ክረምቶች 100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ መመህራን የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱንም ሚኒስትር ዴኤታዋ አመላክተዋል።
በመራኦል ከድር