በተጠባቂ ጨዋታዎች የሚመለሰው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ …
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 8ኛ ሳምንቱ ላይ የደረሰው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከሀገራት ጨዋታዎች በኋላ ዛሬ ሲመለስ በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡
በውድድር ዓመቱ ጥሩ ጅማሮ ላይ የማይገኘው ኖቲንግሃም ፎረስት ቀን 8 ሰዓት ከ30 በሜዳው ቼልሲን በሚያስተናግድበት ጨዋታ የሊጉ 8ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ይጀምራል፡፡
ኖቲንግሃም ፎረስት እስካሁን በሊጉ ካደረጋቸው 7 ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ሲያሸንፍ በሁለቱ አቻ ተለያይቶ በአራቱ ተሸንፎ አምስት ነጥብ በመያዝ 17ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በአሰልጣኝ ኢንዞ ማሬካ የሚመራው ቼልሲ በበኩሉ በሊጉ ካደረጋቸው 7 ጨዋታዎች በሶስቱ ድል ሲቀናው በሁለቱ አቻ ተለያይቶ በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች በመሸነፍ በ11 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በ7ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ሊቨርፑልን ያሸነፈው ቼልሲ አሸናፊነቱን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባል፡፡
በሌላ ጨዋታ አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ በአሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ የሚመራው ማንቼስተር ሲቲ በሜዳው ኢትሃድ ኤቨርተንን ያስተናግዳል፡፡
ያለፉትን ሁለት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች በድል የተወጣው ማንቼስተር ሲቲ በውድድር ዓመቱ በሊጉ እስካሁን ካደረጋቸው 7 ጨዋታዎች አራቱን ሲያሸንፍ በአንዱ አቻ ተለያይቶ በሁለቱ ደግሞ ተሸንፏል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ማንቼስተር ሲቲ አራቱን ሲያሸንፍ በአንዱ አቻ ተለያይተዋል፡፡
ሰንደርላንድ ከወልቭስ፣ ክሪስታል ፓላስ ከቦርንማውዝ፣ በርንሌይ ከሊድስ ዩናይትድ እንዲሁም ብራይተን ከኒውካስል ዩናይትድ በተመሳሳይ አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
ወደ ክራቨን ኮቴጅ በማቅናት ከፉልሃም ጋር ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ የሚጫወተው የሊጉ መሪ አርሰናል በሊጉ ካደረጋቸው 7 ጨዋታዎች አምስቱን ሲያሸንፍ በአንዱ ተሸንፎ በአንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይቷል፡፡
በ16 ነጥብ ሊጉን እየመራ የሚገኘው በአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ የሚመራው አርሰናል መሪነቱን ለማስጠበቅ ይፋለማል፡፡
የሊጉ ጨዋታ ነገ ሲቀጥል በሊጉ ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን የተሸነፈው ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ሮድ 12 ሰዓት ከ30 ላይ ማንቼስተር ዩናይትድን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጠበቃል።
በውድድር ዓመቱ በሊጉ ካደረጋቸው 7 ጨዋታዎች በአምስቱ ድል ሲቀናው በሁለቱ የተሸነፈው ሊቨርፑል ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርገው ፍልሚያ ይጠበቃል፡፡
ማንቼስተር ዩናይትድ በበኩሉ ካደረጋቸው 7 የሊጉ ጨዋታዎች ሶስቱን አሸንፎ በአንዱ አቻ ተለያይቶ በሶስቱ ሽንፈት ገጥሞታል፡፡
በአሰልጣኝ ሩበን አሞሪም የሚመራው ማንቼስተር ዩናይትድ በሊጉ ተከታታይ ጨዋታውን ለማሸነፍ ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ሊቨርፑል ሁለቱን ሲያሸንፍ ማንቼስተር ዩናይትድ በአንዱ ድል አድርጎ በሁለቱ ደግሞ አቻ መለያየታቸው ይታወሳል፡፡
ከዚህ ተጠባቂ ጨዋታ አስቀድሞ ቀን 10 ሰዓት ላይ ቶተንሃም ሆትስፐር ከአስቶንቪላ ይጫወታል።
የ8ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ሰኞ ምሽት ዌስትሃም ዩናይትድን ከብሬንትፎርድ በማገናኘት ይጠናቀቃል፡፡
በወንድማገኝ ፀጋዬ