Fana: At a Speed of Life!

አስራት ኃይሌ ጎራዴው ሲታወስ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ደማቅ አሻራ ፅፈው ካለፉ ሰዎች መካከል ነው አስራት ኃይሌ ጎራዴው፡፡

ለእግር ኳስ ልዩ ፍቅር የነበረው አስራት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ምንም ሳይሰስት ሁሉን ነገር ያደረገ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከተ ልዩ ሰው ነበር።

አስራት ኃይሌ በተጨዋችነት እና በአሰልጣኝነት ዘመኑ በነበረው ትጋት እና ታታሪነት ሁሌም የሚመሰገን ጠንካራ የእግር ኳስ ሰው እንደነበር ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ለግማሽ ምዕተ ዓመት በዘለቀው የስራ ዘመኑ፣ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከተጫዋችነት ጀምሮ በዋና አሰልጣኝነት እና በተለያዩ ሚናዎች አገልግሏል፡፡

በሰላማዊ ንግግሮቹ እና በራስ የመተማመን መንፈስ የሚታወቀው አስራት፤ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ በማበርከት በተጫዋቾች የተደነቀ እና በህዝብ የተወደደ ነበር።

አስራት ለጨዋታ ያለው ቁርጠኝነት እና ታታሪነት ከዘመን ዘመን የሚነገር ለትውልድም የሚተላለፍ ትልቅ አሻራ አኑሮ ያለፈ ስፖርተኛ ነው፡፡

ከመስከረም ኮከብ የጀመረው የአስራት የእግር ኳስ ሕይወት፤ በርካታ ታሪክ እስከሰራበት ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድረስ የተጓዘ ነው፡፡

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዘጠኝ ዓመታት የተጫወተ ሲሆን በፈረንጆቹ 1976 የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተሳተፈው የዋልያዎቹ ስብስብ አባል ነበር።

ወደ አሰልጣኝነት ከገባ በኋላ የአስራት የስኬት ታሪኩን ከፍ አድርጎ በማስቀጠል በተለይም 12 ዓመታትን በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ስኬታማ የአሰልጣኝነት ጊዜ አሳልፏል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከተመለከታቸው ምርጥ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞ መካከል የሚጠቀሰው አስራት ኃይሌ ጎራዴው፤ በአሰልጣኝነት ዘመኑ ከ34 በላይ ዋንጫዎችን በማንሳት ብቃቱን እና ትጋቱን በማሳየት ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ስኬት የተጎናፀፈ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በአሰልጣኝነት እየመራ የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን መሆኑ ይታወሳል፡፡

አስራት ኃይሌ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ሁሌም ሲታወስ የሚኖር አሻራ ማሳረፍ የቻለ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ባለውለተኞች መካከል ግንባር ቀደም ነው፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከተመለከታቸው በእግር ኳሱ ብዙ ታሪክ ከሰሩት መካከል አንዱ የሆነው አስራት ኃይሌ ጎራዴው በዛሬዋ ዕለት ጥቅምት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው፡፡

በወንድማገኝ ፀጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.