ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ጉባኤ እንድታስተናግድ ተሳታፊ ሀገራት ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ጉባኤ (ኮፕ32) እንድታስተናግድ ተሳታፊ ሀገራት ተስማሙ ፡፡
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም በርካታ ተግባራትን እያከናወነች ሲሆን፥ 32ኛውን ጉባኤ ለማስተናገድ ባለፈው መስከረም ወር ጥያቄ አቅርባለች፡፡
በብራዚል ቤለም እየተካሄደ በሚገኘው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ጉባኤ (ኮፕ30) ተሳታፊ ሀገራት የኢትዮጵያን ጥያቄ በመርህ ደረጃ መቀበላቸው ተገልጿል፡፡
የኮፕ30 ጉባኤ ፕሬዚዳንት አንድሬ ኮሪያ ዶ ላጎ የጉባኤው ተሳታፊ ሀገራት ሁነቱን እንድታስተናግድ መስማማታቸውን ገልጸው፥ በዛሬው ዕለት በይፋ ኃላፊነቱን ትቀበላለች ነው ያሉት፡፡
በሌላ በኩል በቀጣዩ ዓመት የሚካሄደውን 31ኛውን ጉባኤ ለማስተናገድ ቱርክ እና አውስትራሊያ ጥያቄ ማቅረባቸው የተገለጸ ሲሆን፥ እስካሁን ውሳኔ ላይ አልተደረሰም ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡