Fana: At a Speed of Life!

በጎንደር ከተማ ወድቆ ያገኙትን አይፎን ስልክ ለባለቤቱ የመለሱት እናት

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጎንደር ከተማ ነዋሪዋ ወ/ሮ አገኘሁሽ አሰፋ በጽዳት ባለሙያነት ተቀጥረው መስራት ከጀመሩ 9 ዓመት ሆኗቸዋል።
ከዚህ ስራ በሚያገኙት አነስተኛ ደመወዝም ቤተሰባቸውን ያስተዳድራሉ።
ወ/ሮ አገኘሁሽ አሰፋ ዛሬ ጠዋት ከተራ እና ጥምቀት የሚከበርበትን ስፍራ በማጽዳት ተግባር ላይ ሳሉ አይናቸው መሬት ላይ የወደቀ እጅግ ዘመናዊ እና ውድ የሆነ አይፎን ስልክ ላይ ያርፋል።
ስልኩን አንስተው ባለቤቱ እስኪደውል መጠባበቅ ይጀምራሉ።
ከዚያም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ስልኩ ጠራ፤ ፈጥነው ስልኩን ሲያነሱትም ‘ሰላም እንዴት ነዎት እመቤት ያገኙት ስልክ እኔ የማስጎበኛቸው እንግዳ ስልክ ነው” የሚል መልዕክት ይሰማሉ።
ወይዘሮዋም እምነት ጠባቂ መሆናቸውን በሚገልጽ አኳኋን በተረጋጋ መንፈስ ‘ባለቤቱ ደውሎ ስልኩን ለመመለስ ተዘጋጅቼ እየተጠባበቅሁ ነው’ የሚል ምላሽ ይሰጣሉ።
ይህንን ምላሽ የሰሙት የስልኩ ባለቤት ብዙ ነገራቸው ከስልካቸው ጋር በመያያዙ መደናገጥ ውስጥ ገብተው የነበሩት የውጭ ሀገር ዜጋ ደስታቸው እጅግ ከፍተኛ ሆነ።
ከጥቂት ደቂቃ በኋላም ስልኩ የጠፋባቸው እንግዳ ወይዘሮ አገኝሁሽ ወደሚሰሩበት ቦታ ደርሰው ስልካቸውን ተረከቡ።
ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ በተመሳሳይ ሁኔታ ወድቆ ያገኙትን ስልክ በታማኝነት ለባለቤቶቹ የመለሱት ወ/ሮ አገኘሁሽ አሰፋ፤ በአሁኑ ገጠመኝ ጥምቀትን በጎንደር ሊባረክ የመጣ የውጭ ሀገር ሰው ሊከፋው አይገባም በሚል በፍፁም መታመን ለባለቤቱ በመመለሴ ደስተኛ ነኝ ብለዋል።
ያልደከሙበትን የራስ ለማድረግ ማሰብ ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑን በመግለጽ፤ ከምንም በላይ ለራስ መታመን በፈጣሪ ዘንድ የተወደደ ተግባር ነው በማለት ተናግረዋል።
ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር ከመሰሎቹ ጋር የመጣው አሜሪካዊው ጃፍ በጉብኝት ወቅት ምስል ለማስቀረት ስልኩን ሲፈልግ ነበር ስልኩ እንደወደቀበት ያወቀው።
ነገር ግን ወደ ስልኩ በሚደውሉበት ወቅት ወ/ሮ አገኘሁሽ አሰፋ ቀና ምላሽ በመስጠት ስልካቸውን የመለሱላቸው በመሆኑ እጅግ በመደሰት ከፍተኛ ምስጋና ማቅረቡን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ገልጸዋል።
በፍጹም ታማኝነት የተመለሰለት ስልክ በርካታ መረጃ መያዙን በመጥቀስ፤ ጥምቀት የማይረሳ ገጠመኝ እንደተወላቸው ተናግረዋል።
በምናለ አየነው
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.