Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ዜጎች ከስኳር ሕመም ጋር ይኖራሉ – ማህበሩ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ዜጎች ከስኳር ሕመም ጋር ይኖራሉ አለ የኢትዮጵያ ስኳር ሕመም ማህበር።

የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጌታሁን ታረቀኝ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ የስኳር ሕመም በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለፉት ዓመታት በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ መጥቷል፡፡

የስኳር ሕመም በሰውነታችን ውስጥ ሃይል ሰጪ ምግቦች ወይም የስኳር ምግቦች ልመት ሥርዓት ውስጥ ወደ ሕዋስ እንዲገባ የሚያደርገው ሆርሞን (ኢንሱሊን) አለመመረት ወይም አለመሥራት ሲከሰት የሚፈጠር ነው።

በኢትዮጵያ እድሜያቸው ከ20 እስከ 79 ዓመት የሆኑ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ሰዎች ከስኳር ሕመም ጋር አብረው እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመላክታሉ ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በስኳር ሕመም የሚያዙ ሰዎች ብዛት እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው÷ በተለይም ትክክል ባልሆነ የአኗኗር ዘይቤ ሳቢያ የሚከሰተው አይነት ሁለት የስኳር ሕመም እየተስፋፋ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን አብዝቶ መመገብ፣ ከፍተኛ የስኳር እና የስብ መጠን ያላቸውን ምግቦች መመገብ፣ ውፍረት መጨመር፣ አልኮል መጠጣት እና ሲጋራ ማጤስ የስኳር ሕመም መንስኤዎች ናቸው፡፡

ለዕይታ ማጣት፣ ለኩላሊት ሕመም፣ ከአደጋ ጋር ላልተያያዘ የእግር ሕመም፣ ለልብ ሕመም እና ሌሎች ሕመሞች ዋነኛ መንስዔው የስኳር በሽታ መሆኑንም አስረድተዋል።

በአሁኑ ጊዜ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ውስጥ የስኳር ሕመም በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ ያደርገዋል ያሉት ዶ/ር ጌታሁን÷ ወደፊትም የታማሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር መረጃዎች ያመላክታሉ ነው ያሉት፡፡

ሕብረተሰቡ ከስኳር ሕመም ጋር ተያይዞ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ከጤና ሚኒስቴር ጋር የግንዛቤ መፍጠር ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ጤናማ የሆነ የአኗኗር ዘይቤን በመከተል አይነት 2 የስኳር ሕመምን እስከ 80 በመቶ መከላከል እንደሚቻል አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ እና አመጋገብን ማስተካከል በተለይም ልጆች የሚመገቡትን በፋብሪካ የተቀነባበሩ ከፍተኛ የስኳርና ስብ መጠን ያላቸውን ምግቦች መቀነስ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በነገው ዕለት የሚከበረውን የስኳር ሕመም ቀን አስመልክቶም ሕብረተሰቡ ስለ ስኳር ሕመም ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ የሚያስችሉ የተለያዩ መርሐ ግብሮች እንደሚከናወኑ አመልክተዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.