በክልሉ በማዕድን ዘርፍ የሚገኘውን ጥቅም የሚያሳድጉ ውሳኔዎች ተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማዕድን ግብረ ሃይል በዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግና ሕገ ወጥ ድርጊቶችን መቆጣጠር የሚያስችሉ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
ግብረ ሃይሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን በተገኙበት ነው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ያሳለፈው፡፡
በክልሉ የወርቅ ምርት እያደገ ቢመጣም ምርቱ ሙሉ በሙሉ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዳይገባ የሚያደርጉ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ግብረ ሃይሉ አመልክቷል፡፡
የወርቅ ምርት ሙሉ በሙሉ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዳይገባ የሚያደርጉ አካላት በክልሉና በሀገር ላይ ትልቅ ክህደት እየፈጸሙ መሆኑንም ገምግሟል፡፡
ግብረ ሃይሉ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ሥርዓት ለማስያዝ የተለየ ስልት ቀይሶ እንደሚሠራ ነው አጽንኦት የሰጠው፡፡
ሕገ ወጥነትን በሚያባብሱ አካላት ላይ የተጀመረው ክትትል እንደሚጠናከርና በቀጣይም ከድርጊታቸው በማይቆጠቡ አካላት ላይ ርምጃ እንደሚወስድ አስገንዝቧል።
ከማዕድን ልማት ሥራው ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሰው እንቅስቃሴ መኖሩን ግብረ ሃይሉ በውይይቱ ላይ አንስቷል፡፡
በማዕድን ልማት ሽፋን የክልሉ ጸጥታ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ እንቅስቃሴዎችን በመከታተል የቁጥጥር ሥራውን እንደሚያጠናክርም የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡