በኦሮሚያ ክልል ከ4 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ ሰብል ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በ2017/18 ምርት ዘመን በመኸር ከለማው ከ11 ሚሊየን ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን ከ4 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የሰብል ምርት ተሰብስቧል አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ፡፡
የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር እንደሻው ጀማና ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ በክልሉ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የተሰበሰበ ሰብል ተወቅቶ 54 ሚሊየን ኩንታል ምርት ተገኝቷል።
በክልሉ በአጠቃላይ በመኸር ወቅት ከ11 ሚሊየን ሄክታር መሬት በላይ በሰብል መሸፈኑን አስታውሰው፤ እስካሁን ከ4 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የደረሱ ሰብሎች ተሰብስበዋል ብለዋል፡፡
በክልሉ የምርት ብክነት እንዳይኖር የደረሱ ሰብሎችን በኮምባይነር የመውቃት እና የመሰብሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አቶ እንደሻው ገልጸዋል፡፡
አርሶ አደሮች የደረሱ ሰብሎችን ከብክነት በጸዳ መንገድ የመሰብሰብ ስራውን በአግባቡ እንዲከውኑ የግብርና ባለሙያዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እገዛ እንደሚያደርጉም አስገንዝበዋል።
በአቤል ነዋይ