Fana: At a Speed of Life!

የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት… የእርቅ እና የትህትና በዓል

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትልቅ ስፍራ ሰጥታ ከምታከብራቸው አበይት በዓላት አንዱ ነው፡፡

በዓሉ በታሕሣሥ ወር በ29ኛው ቀን የሚከበር ሲሆን፥ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ዮሐንስ ታሕሣሥ 28 ይከበራል፡፡

ለአዳም የተገባው የድህነት የተስፋ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነቢያት እጅግ የሚናፍቁትና ተስፋ የሚያደርጉት የኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለድ እንደሚፈጸም አምነው በጾም በጸሎት ተወስነው አምላክ ሰው የሚሆንበትን ጊዜ እያሰሉ ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡

ቤተክርስቲያኗ አስቀድሞ እግዚአብሔር በነቢያት አድሮ የተናገረው የትንቢት ቃል ይፈጸም ዘንድ የክርስቶስን መወለድ በመጾም ጭምር ይጠብቁ የነበሩ ነቢያትን አብነት አድርጋ ከልደት በዓል በፊት 44 ቀናትን በጾም ታሳልፋለች፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በእግዚአብሔር እና በሰው መካከል እርቅ የተፈጸመበት ታላቅ የትህትና በዓል ነው፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መምህር የሆኑት መጋቤ ብሉይ አዕምሮ ዘውዴ ይህንን ሲያስረዱ፥ የአምላክን ትዕዛዝ ተላልፎ ያጠፋው የሰው ልጅ ሆኖ ሳለ እግዚአብሔር ከሰማያት ወርዶ የሰውን ስጋ የነሳው እርቅ ሊፈጽም መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ልደቱ እርቅ የተፈጸመበት፣ የጥል ግድግዳ የፈረሰበት፣ ሰውና መላዕክት በአንድነት እግዚአብሔርን ያመሰገኑበት የፍቅር፣ የሰላምና የእርቅ በዓል መሆኑን ነው የሚገልጹት፡፡

የእግዚአብሔር እና የሰው፣ የሰው እና መላዕክት ብሎም የስጋና ነፍስ እርቅ የተፈጸመበት በዓል ነው፡፡ ከእርቅ ባሻገር የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የትህትና በዓል መሆኑንም መጋቤ ብሉይ አዕምሮ ዘውዴ ያስረዳሉ፡፡

አንዱ የትህትናው መገለጫ የማይራበው፣ የማይጠማው አንዳች ያልጎደለበት ልዑል እግዚአብሔር የጎደለበትን ዓለምና የሰውን ልጅ ጉድለት ሊሞላ ከሰማያት ወርዶ በከብቶች በረት መወለዱ ነው፡፡

ልብሱ እሳት ሁለንተናው እሳት የሆነ አምላክ በእንስሳት ማደሪያ በተወለደ ጊዜ የብርድ ወራት ስለነበረ በእንስሳቱ ትንፋሽ መሞቁ የተናቁትን የሚያከብር የትህትና አባት እንደሆነ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ በተናቀ ጠባብ በረት ውስጥ መወለድ ከትህትናው ባሻገር የሰውን ልጅ ከተናቀችው ዓለም አስወጥቶ ወደ ዘለዓለም ህይወት፥ ወደ ሰፊዋ መንግስተ ሰማያት ማስገባት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ መላዕክት ከሰማያት መጥተው ከእረኞች ጋር ምስጋና ማቅረባቸውን ቅዱስ መጽሐፍ ይናገራል፡፡ ይህም የክርስቶስ ልደት አከባበር የተጀመረበት መሆኑን ነው መጋቤ ብሉይ አዕምሮ ዘውዴ የሚገልጹት፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም ይህንን አብነት በማድረግ በዋዜማው ስርዓተ ማህሌት በማከናወን በልዩ ልዩ ኃይማኖታዊ ሥነሥርዓቶች በየዓመቱ ታከብራለች፡፡

ህዝበ ክርስቲያኑ ይህንን ታላቅ በዓል ሲያከብር ከምድራችን የራቀውን ፍቅርና ሰላም ለመመለስ በመረዳዳት፣ በትህትና እና ለአምላክ ምስጋና በማቅረብ ሊያከብሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በተጨማሪ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና በኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተክርስቲያናት በዝማሬና በልዩ ልዩ ሀይማኖታዊ ስነስርዓቶች በድምቀት ይከበራል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.