በአፍሪካ የሙዚቃ መድረክ ላይ እየደመቁ የመጡት ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች…
አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች በአፍሪካ የሙዚቃ እና የኪነጥበብ መድረኮች ላይ አሻራቸውን ማሳረፋቸውን ቀጥለዋል፡፡
አርቲስቶቹ በተለያዩ የሽልማት መድረኮች ላይ በአኅጉራዊ እውቅና እየተበረከተላቸው ይገኛል።
በናይጀሪያ ሌጎስ ከተማ በተካሄደው የሁሉም አፍሪካ የሙዚቃ ሽልማቶች (አፍሪማ) ላይ የኢትዮጵያ ባለተሰጥኦ አርቲስቶች በተለያዩ ምድቦች ሽልማት አግኝተዋል።
በዚህ የሽልማት መድረክ ላይ ኢትዮጵያዊቷ ድምጻዊት ቬሮኒካ አዳነ በምርጥ የአፍሪካ ባህላዊ ሙዚቃ አርቲስት ቡድን ዘርፍ ሽልማትን በማሸነፍ የሀገሯን ስም በሙዚቃው ኢንዱስትሪው ውስጥ ከፍ ብሎ እንዲታይ ማድረግ ችላለች።
እንዲሁም ኢትዮጵያዊቷ ድምጻዊት ዊሃ “ድማማ” በተሰኘው የሙዚቃ ሥራዋ በምርጥ የአፍሪካ ዳንስ እና ኬሮግራፊ ዘርፍ ሽልማት አሸናፊ መሆን ችላለች።
በተጨማሪም በአፍሪካ ጃዝ ምርጥ የአፍሪካ አርቲስት ሽልማት የኢትዮጵያው ሃዲንቆ የሙዚቃ ቡድን ማሸነፍ ችሏል።
የሽልማት መድርኩ ኢትዮጵያ ከባህላዊ የሙዚቃ ዘውግ ባሻገር በሌሎች ዘውጎች እና ዘርፎች ላይ ያላትን ተወዳዳሪነት ያስመሰከረችበት ሲሆን÷ ከዚህ ባለፈ በሌሎች የሙዚቃ መድረኮች ላይ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች ደምቀው በመታየት ላይ ይገኛሉ።
በተለይም ከዚህ በፊት በምስራቅ አፍሪካ የጥበብ መድረክ ድምጻዊት ቬሮኒካ አዳነ የዚኮሞ አፍሪካ ሽልማቶች ላይ በልዩ ልዩ ዘርፎች ላይ መመረጥ መቻሏ የኢትዮጵያ ባህላዊ እና ዘመናዊ ሙዚቃዎች ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው እየጨመረ መምጣቱን አጉልተው የሚያሳይ ነው።
በፈረንጆቹ 2014 በተመሰረተው እና በአፍሪካ የሙዚቃ ዘርፍ ላይ ትልቅ ቦታ በሚሰጠው አፍሪማ የሽልማት መድረክ ላይ ኢትዮጵያውያኑ አሸናፊ መሆናቸው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ እድገት እና ተደማጭነት ያጠናክራል፡፡
ከዚህ ባለፈም አርቲስቶቹ የዓለም የመግባቢያ ቋምቋ በሆነው ሙዚቃ ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው መቀጠሉ እና የሚያገኟቸው ሽልማቶች የበለጠ ተቀባይነታቸው እንዲጨምር ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል።