Fana: At a Speed of Life!

የሸኮ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ቲከሻ ቤንጊ” በዓል እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሸኮ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ቲከሻ ቤንጊ” የምስጋና በዓል በተለያዩ ባህላዊ ሁነቶች በሸኮ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።

በበዓሉ ላይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳደር ነጋሽ ዋጌሾን (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎች፣ የብሔረሰቡ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የሸኮ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ቲከሻ ቤንጊ” የምስጋና በዓል ሲሆን፤ “ቲከሻ” የሚለው ቃል ትርጓሜው ምስጋና ሲሆን “ቤንጊ” የሚለው ቃል ደግሞ በዓል የሚለውን ትርጓሜ ይይዛል።

ቲከሻ ቤንጊ የሸኮ ህዝቦች አዝመራውን ከንፋስ እና በረዶ እንዲሁም ከዋግ በሽታ ጠብቆ ላቆየላቸው ፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርቡበት ለዘመናት ያዳበሩት የባህል እሴት ነው።

ሸኮዎች ቲከሻ ቤንጊን የሚያከብሩት ቡናና ቅመማቅመም እንዲሁም የደረሰውን እህል ሰብስበው ወደ ጎተራ በሚያስገቡበት በጥር ወር ነው።

እህል ከተሰበሰበ በኋላ ሸኮዎች የጎሳ መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት እህሉን ጠብቆ ላደረሰ ፈጣሪ ምስጋናን በማቅረብ ወደ አዲስ የዘመን ምዕራፍ መሻገራቸውን ያበስራሉ፡፡

ከበሽታና ከቸነፈር ተጠብቀው ደስታ ወደሞላበት የአዝመራ ወቅት ወይም አዲስ ምዕራፍ በመሻገራቸው ምስጋና የሚያቀርቡበትና ለመጪው ጊዜ ማማር አባቶች የሚርቁበት ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.