Fana: At a Speed of Life!

ባህላዊ እሴቶችና አብሮነትን የሚያጎላው የ“ዎናንካ አያና” በዓል

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቡርጂ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ዎናንካ አያና” በዓል የሕዝብን ባህላዊ እሴቶችና አብሮነትን በማጉላት አሰባሳቢ የወል ትርክትን የሚያጠናክር በዓል ነው አለ የቡርጂ ዞን አስተዳደር።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ትንሳኤ ዮሐንስ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ “ዎናንካ አያና” የሕዝብን ባህላዊ እሴቶች፣ አብሮነትና የግብርና ልማት ተሳትፎን የሚያጠናክር፣ አሰባሳቢ የወል ትርክትን የሚያጎላ፣ የአግነይሼ (የይቅርታ)፣ የምስጋና (ኤባ) ሥርዓትን አቅፎ የያዘ ሕዝባዊ የአደባባይ በዓል ነው።

በዓሉ የበርካታ ቱሪስቶችን ትኩረት እየሳበ መሆኑን ጠቅሰው÷ ድንቅ እሴት የያዘ በመሆኑ ለዓለም በማሳየት ለቱሪዝም ሀብት መጠቀም ይገባል ብለዋል።

የዞኑ ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ ካሳ አለማየሁ በበኩላቸው÷ መንግሥት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለቱሪዝም ዘርፍ የሰጠው ትኩረት እንደ “ዎናንካ አያና” ያሉ ቱባ ባህሎችን የያዙ በዓላት ለዓለም እንዲተዋወቁ እድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

የብሔረሰቡ መገለጫ የሆኑትን የዎና በዓል፣ የላጎ ግርዝ ሥርዓት፣ የኦልቾ ሽምግልናና የአግነይሼ የመሳሰሉ አስተሳሳሪ እሴቶችን በጋራ በማልማት ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገትና ለሀገር ብልጽግና ማዋል አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዎናንካ አያና በዓል የቡርጂ ብሔረሰብ አለመግባባቶችን በንግግር በመፍታት አብሮ ለመልማትና ሰላማዊ ኑሮ ለመኖር የሚያስችል በፍቅር የሚደመሩበት የጋራ በዓል ነው ያሉት ደግሞ የቡርጂ ብሔረሰብ የጋርንካ ኦልቾ መሪ አንሽ ብልሁን ጮንዴ ናቸው።

የቡርጂ ብሔረሰብ የማንነት መገለጫ፣ የባህልና እሴቱ መድመቂያ፣ የጠንካራ ስራ ወዳድነት ተምሳሌት፣ የአንድነትና የፍቅር መስበኪያው የሆነው ዎና በዓል በየዓመቱ የካቲት 6 ቀን በድምቀት ይከበራል።

ዘንድሮም በዓሉ የብሔረሰቡ ተወላጆች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በፓናል ውይይቶች፣ በባህል ፌስቲቫልና ኤግዚቢሽን፣ በአግነይሼ ምርቃት ሥርዓት እና በተለያዩ ዝግጅቶች ቡርጂ ሶያማ ከተማ ላይ እንደሚከበር ተገልጿል።

በመለሰ ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.