የሌማት ትሩፋት ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ተደማሪ አቅም ሆኗል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ዘላቂ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ፖሊሲ ትግበራ ተደማሪ አቅም ሆኗል አሉ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ የሌማት ትሩፋት መንግስት ለዜጋና ለሀገር ያለውን ክብር ያሳየበት ልዩ እሳቤና ትግበራ ነው ብለዋል፡፡
መርሐ ግብሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የምናብ ልህቀት ፈልቆ የተጀመረ መሆኑን አስታውሰው፥ የብዙ ቤተሰብን ሕይወት መቀየር ችሏል ነው ያሉት፡፡
የሌማት ትሩፋት ለዘመናት ጸጋ ሆነው ያልታዩ ጓሮዎችን የልማት ከባቢ አድርጓል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ መንግስት የሌማት ትሩፋትን ዘላቂ የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ፖሊሲ ትግበራ ተደማሪ አቅም ማድረጉን አንስተዋል፡፡
የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽነት በሽታ መከላከልን ካስቀደመው የኢትዮጵያ የጤና ፖሊሲ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ጠቁመው፥ የመደመር እሳቤ ያፈለቀው የፈጠራ ተግባር የእንስሳት ተዋጽኦ በአግባቡ ወደ ሌማታችን እንዲመጣ አስችሏል ብለዋል፡፡
የሌማት ትሩፋት ከከበረው የሰዎች ሕይወትና ጤና፣ ከትልቁ የሀገር መልክና ክብር እንዲሁም ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ርዕይ ጋር የተሳሰረ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፥ በሌማት ትሩፋት በትጋት የሰሩ ክንዶች ሌማታቸውን አትረፍርፈዋል ነው ያሉት፡፡