የአፋር ህዝብ ዕሴት የሆነውን “ማድዓ” ባህላዊ የዳኝነት ስርዓትን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) “ማድዓ” የአፋር ማህበረሰብ ሁሉን አቀፍ መተዳደሪያ ማዕቀፍ ሲሆን በማህበረሰቡ እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የተጣላን የሚያስታርቅ የአብሮነት ዕሴት የሆነ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ነው።
የአፋር ባህላዊ ዕሴት የሆነውን “ማድዓ” በዘመናዊ መልኩ ከመጠቀምም በላይ በሳይንስ ጥናት የተደገፈ ሆኖ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ ያለመ ሀገራዊ ኮንፍረንስ በሰመራ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ማድዓ ከመደበኛው የሕግ አገልግሎት ጎን ለጎን በአፋር ህዝብ ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት ያለው እና መንግሥትም ዕውቅና የሰጠው ባህላዊ ሥርዓት መሆኑ ተገልጿል።
የማድዓ ዋነኛ ግብ ሰውን መቅጣት ብቻ ሳይሆን፣ ተበዳይ ካሳ እንዲያገኝ ማድረግ እና በሁለቱ ወገኖች መካከል ዘላቂ ሰላም ማውረድ በመሆኑ ለትውልድ ማሻገር እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
“ማድዓ” በሁለት ወገኖች መካከል ለሚፈጠር ግጭት የቅርብ ተመልካች ወይም ጉዳዩን ቀድሞ የሰማው አካል ተጠያቂ የሚያደርግ ሲሆን ለዘመናት በቃል ሲተላለፍ የቆየ፣ ነገር ግን እጅግ የተዋቀረ ሥርዓት ያለው ባህላዊ ሕግ ነው።
ሕጉን የሚተረጉሙትና ፍርድ የሚሰጡት በሕግ ዕውቀታቸውና በታማኝነታቸው የተመረጡ አዛውንቶች ሲሆኑ ከግል ጉዳዮች፣ ከጋብቻ፣ ከውርስ ጀምሮ እስከ ከባድ ወንጀሎች እና የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ድረስ ሁሉንም የሕይወት ዘርፎች የሚያስተዳድሩ ህጎችን አካትቷል።
በኮንፍረንሱ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፣ የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ መንግሥት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የጎሣ መሪዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የአፋር የማድዓ አባቶች እና የዘርፉ ተመራማሪዎች ተገኝተዋል።
በኃይለኢየሱስ ስዩም