Fana: At a Speed of Life!

ከዓለም አቀፍ የቱሪዝም መዳረሻዎች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ…

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ በሰራቻቸው ስራዎች ከዓለም የበለጸጉ መዳረሻዎች አንዷ መሆን ችላለች፡፡

እያደጉ በመጡ ዓለም አቀፍ ጉዞዎች በፈረንጆቹ 2025 ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ቱሪስቶች ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት ተጉዘዋል፡፡

አውሮፓ በዓለም አቀፍ ቱሪስቶች በብዛት የሚጎበኝ ቢሆንም በፈረንጆቹ 2024 ፈጣን ዕድገት ያስመዘገቡት መዳረሻዎች የተለመዱ ሀገራት አይደሉም፡፡

በዚህም ብራዚል 37 በመቶ፣ ግብፅ 20 በመቶ፣ ኢትዮጵያ 15 በመቶ፣ ቡታን 30 በመቶ፣ ሲሸልስ 13 በመቶ ዕድገት ማስመዝገባቸውን የቢቢሲ መረጃ አመልክቷል።

በአሁኑ ጊዜ ተጓዦች ወደ ልዩ ባህል፣ መልክዓ ምድሮች፣ የግኝት እድሎች እና ጠንካራ ማንነት ያላቸው ሀገራትን መጎብኘት እንደሚመርጡ ነው የተገለጸው፡፡

በዘርፉ በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ በርካታ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ሆናች፡፡

ኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ ትኩረት ሰጥታ በመስራት የሚታይ ለውጥ በማምጣት የቱሪስት ፍሰትን መጨመር ችላለች፡፡

ኢትዮጵያ በተደራሽነት እና በተጓዥ እምነት ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በስፋት ሰርታለች፡፡

በ2025 ኢትዮጵያን ይጎብኙ ንቅናቄ መጀመርን ጨምሮ አዳዲስ ሆቴሎች እና የተሻሻሉ አገልግሎቶች መስፋፋታቸው ተመራጭ የቱሪዝም መዳራሻም አድርጓታል፡፡

በዚህም ምክንያት ለብዙ ዓመታት ዕቅዳቸውን ያራዘሙ ጎብኝዎች በየጊዜው መመላለሳቸውን ጨምሮ በኢትዮጵያ የቆይታ ጊዜያቸውን በማራዘም ላይ ይገኛሉ፡፡

የቱሪስቶች ፍሰት ከፈረንጆቹ 2024 እስከ 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ የ40 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን÷ የደህንነት መሻሻል እና ኢትዮጵያ በዘርፉ የሰራቻቸው ስራዎች ለዚህ ዕድገት ትልቁን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

በዚህ ዓመት ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ከ20 በላይ የውጭ ሀገራት ትምህርት ቤቶች ዝግጅት እያደረጉ ሲሆን÷ ይህም አዳዲስ የጉዞ ፍላጎቶች መኖራቸውን ያሳያል፡፡

ኢትዮጵያ በአርኪዮሎጂ፣ በአንትሮፖሎጂ እና የተፈጥሮ ታሪክን በስፋት ለመለማመድ ከዓለማችን እጅግ የበለጸጉ መዳረሻዎች አንዷ ሆናለች፡፡

የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የአክሱም ሐውልት እና የሰሜን ተራሮችን ጨምሮ ሌሎች በኢትዮጵያ የሚገኙ በርካታ የቱሪዝም ስፍራዎች ጎብኝዎችን ይስባሉ፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.