Fana: At a Speed of Life!

በ2012 በጀት አመት 787 የበይነ መረብ ጥቃቶች ከሽፈዋል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 18፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2012 በጀት አመት በተለያዩ ተቋማት ላይ የተቃጡ 787 የሚሆኑ የበይነ መረብ ጥቃት ሙከራዎች ማክሸፉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
 
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ከፍያለው ተፈራ እንዳሉት ከተሰነዘሩ 1 ሺህ 78 በይነ መረብ ጥቃቶች 787 የሚሆኑትን ማክሸፍ የተቻለ ሲሆን፣ 124 የሚሆኑት ደግሞ ምላሽ በመስጠት ሂደት ላይ ሲሆኑ ቀሪዎቹ 167 የሚሆኑት በተለያዩ ምክንያቶች ምላሽ ያልተሰጣቸው ናቸው፡፡
 
ከዚህ ውስጥ 474ቱ በአጥፊ ሶፍትዌሮች ማልዌር የተፈጸሙ ሲሆኑ፣ 288 የድረ-ገፅ ጥቃት፣ 104 የመሠረተ ልማት ቅኝት፣ 188 ወዳልተፈቀደ ሲስተም ሰርጎ መግባት፣ 22 ደግሞ የበይነ መረብ መሠረተ ልማቶችን ሥራ ማቋረጥ እና 2 በበይነ መረብ ማጭበርበር የተሰነዘረ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
 
ጥቃቶቹ የሃገሪቱን ቁልፍ የመሰረተ ልማትና ተቋማት ኢላማ አድርገዉ የተከሰቱ ይገኙበታልም ብለዋል፡፡
 
ክስተቱ ካለፉት አመታት ጋር ሲነጻጸር ቁጥሩ እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ያም ሆኖ በኤጀንሲው የበይነ መረብ ጥቃት አደጋ ዝግጁነት እና ምላሽ መስጫ ዲቪዥን የከፋ ጉዳት ሳያደርሱ ማክሸፍ መቻሉንም ነው የተናገሩት።
 
ጥቃት የደረሰበት ተቋም ቋሚ አድራሻ አለመታወቅ፣ አይፒ የሚለዋወጥ መሆን፣ ተቋማት መረጃው ከተሰጣቸው በኋላ ቸልተኝነት ማሳየት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢንዱስትሪው አዳዲስና ውስብስብ የሆኑ ጥቃቶች መፈጠራቸው እንዲሁም በተቋማትና በግለሰብ ደረጃ የበይነ መረብ ደህንነት እውቀት ግንዛቤ ማነስ ለጥቃቶቹ ምላሽ ለመስጠት የሚደረገውን ሂደት አስቸጋሪ አድርጎታልም ነው ያሉት፡፡
 
የተቋማት ወደ ዲጂታል ዓለም በስፋት መግባት፣ ስለ በይነ መረብ ደህንነት ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን፣ ግለሰቦች መሰረታዊ የተባሉ የበይነ መረብ ደህንነት ቴክኖሎጂን አለመተግበር፣ ህጋዊ ያልሆኑ ሶፍትዌሮችን መጠቀም እና የኮምፒውተር ስርዓቶቻቸውን በበይነ መረብ ደህንነት አለማስፈተሽ ለጥቃቱ መጨመር እንደምክንያት የሚጠቀሱ ናቸዉ ተብሏል፡፡
 
90 በመቶው የሚሆነው ጥቃት በሰዎች የግንዛቤ ጉድለት የሚከሰት መሆኑን ያነሱት አቶ ከፍያለው ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይደርስ ኤጀንሲው ለተለያዩ የመንግስት እና የግል ተቋማት የበይነ መረብ ደህንነት ስልጠናዎችን መስጠቱን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.