ለ16 የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፍቃድ ተሰጥቷል – የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን እስካሁን ለ16 የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፍቃድ ተሰጥቷል አለ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሃና ተኽልቁ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፥ ተቋሙ በተለይም በዚህ ዓመት ለሰነደ መዋዕለ ንዋይ ምዝገባ በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡
በካፒታል ገበያው ውስጥ ለሚሳተፉ ተቋማትና ግለሰቦች ፍቃድ የመስጠትና ቁጥጥር የማድረግ ኃላፊነት የተሰጠው ባለስልጣኑ፥ በቢሊየኖች የሚቆጠር በጀት ያላቸውን ተቋማት መመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።
የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፍቃድ ቁጥር መጨመሩን አንስተው፥ እስካሁን ለ16 የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፍቃድ ተሰጥቷል ነው ያሉት።
የፍቃድ አሰጣጥ ስርዓቱን ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፥ ሰነደ መዋዕለ ንዋያቸውን ያላስመዘገቡ ኩባንያዎች እንዲያስመዘግቡ አሳስበዋል።
ባህር ዳር፣ አምቦ፣ ጅግጅጋ እና አርባምንጭ ከተሞችን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች የካፒታል ገበያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች መካሄዳቸውን አንስተዋል።
ባለስልጣኑ ሁለተኛውን ቀጣናዊ የካፒታል ገበያ ጉባኤ በስኬት ማከናወን ችሏል ነው ያሉት።
በሶስና አለማየሁ