Fana: At a Speed of Life!

የሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን 20ኛ ዓመት የዕረፍት መታሰቢያ ፕሮግራም ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን 20ኛ ዓመት የዕረፍት መታሰቢያ ፕሮግራም በአምቦ ከተማ ተካሂዷል።

የመታሰቢያ ፕሮግራሙን የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀ ሲሆን÷ መነሻውን ከአዲስ አበባ ራስ መኮንን ድልድይ ሰባ ደረጃ የሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን መታሰቢያ ሐውልት ማድረጉ ተመልክቷል።

የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በቀጣይ ከዚህ በተሻለ ሎሬቱን የሚያስታውሱ ስራዎች ይሰራሉ።

ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህንን በህይወት ካጣነው 20 ዓመታት ቢቆጠሩም ለኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ያደረገው አስተዋፅኦ ዛሬም ህያው ያደርገዋል ብለዋል።

የመታሰቢያ ፕሮግራሙ ከመዘከር ባለፈ የሎሬቱን የጥበብ ትሩፋትና በጎ ዐሻራ ለወጣቱ ትውልድ ለማስተላለፍ ያለመ መሆኑን አንስተዋል።

በዝግጅቱ የተሳተፉ አንጋፋና ወጣት የኪነጥበብ ባለሙያዎች በአምቦ ዩኒቨርሲቲ በሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን የተሰየመውን ማዕከል እና በከተማው ያሉ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

በተጨማሪም ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን በተወለዱበት ስፍራ በስማቸው በተሰየመው 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት አካሂደዋል።

ፀሐፈ ተውኔት፣ ገጣሚ እና ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ክፍል እንዲቋቋም በማድረግ፣ ከ35 በላይ ተውኔቶች፣ ግጥሞች እና የተለያዩ መጣጥፎችን በመጻፍ ለኢትዮጵያ የኪነጥበብ ዘርፍ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።

እናት ዓለም ጠኑ፣ ምኒሊክ የመቅደላ ስንብት፣ ሰቆቃው ጴጥሮስ፣ የከርሞ ሰው አስቀያሚ ልጃገረድ፣ እኔም እኮ ሰው ነኝ፣ የእሾህ አክሊል፣ ሀሁ በ6 ወር፣ ዘርአይ ድረስ እና ሌሎችም የሎሬቱ ተጠቃሽ ስራዎቹ ናቸው።

በሲሳይ ኃይሌ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.