Fana: At a Speed of Life!

ስለመራጮች ምዝገባ ዋና ዋና ጉዳዮች

—————————————
በማንኛውም ምርጫ ለመሳተፍ አስቀድሞ በመራጭነት መመዝገብ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡

አንድን ሰው በመራጭነት ለመመዝገብ የሚያበቁት መስፈርቶችና የሚያስፈልጉት ሰነዶች በምርጫ ሕግና እንደ አስፈላጊነቱም በምርጫ ቦርድ በሚወጡ ዝርዝር ደንቦችና መመርያዎች ይቀመጣሉ፡፡

ነገር ግን እነዚህ መስፈርቶች ተገቢና አስፈላጊ በሆነ መጠን ብቻ እንጂ እንድን ሰው ያለ አግባብ ከመራጭነት የሚያገሉ መሆን የለባቸውም፡፡

በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት በማንኛውም ምርጫ፡-
• ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው፣
• በምዝገባው ዕለት ዕድሜው/ዋ 18 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነችና
• ለምዝገባ በቀረበበት የምርጫ ክልል ቢያንስ ለ6 ወራት የኖረ ሰው በመራጭነት ለመመዝገብ ይችላል፡፡

ነገር ግን በአዕምሮ ህመም ምክንያት የመወሰን አቅም የሌለው መሆኑ የሚታወቅ ሰው፣ በፍርድ የተወሰነበትን የእስራት ቅጣት በመፈጸም ላይ ያለ ሰውና የመምረጥ መብቱ በሕግ የተገደበበት ሰው በመራጭነት ለመመዝገብ እንደማይችል በሕጉ ተደንግጓል፡፡

የመራጮች ምዝገባ የሚከናወነው በምርጫው ዓይነት ላይ ተመስርቶ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በሚያወጣው የመራጮች ምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ አማካኝነት ሲሆን የምዝገባ ቦታውም መራጮች በሚኖሩበት ቀበሌ በሚቋቋም የምርጫ ጣቢያ ብቻ ነው፡፡

ሆኖም በአርብቶ አደር አከባቢዎች አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ተንቀሳቃሽ የመራጮች ምዝገባ ማዕከላት በማቋቋም የመራጮችን ምዝገባ ማከናወን ይቻላል፡፡

አንድ ሰው ለመራጭነት በአንድ የምርጫ ጣቢያ መመዝገብ የሚችለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ የራሱ የመራጮች መዝገብ ይኖረዋል፡፡

የመራጮች ምዝገባን በተመለከተ ሁለት ሊታወሱ የሚገባቸው ጉዳዮች፡-
1) የመራጮች ምዝገባ ሊከናወን የሚችለው ቦርዱ በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ብቻ ነው፡፡

2) ቀደም ሲል እንደተገለጸው ለአርብቶ አደር አከባቢዎች በተለየ ሁኔታ ካልተወሰነ በስተቀር ምዝገባው የሚከናወነው መራጮች በሚኖሩበት ቀበሌ በሚቋቋም የምርጫ ጣቢያ ብቻ ነው፡፡

አንድ መራጭ በመራጭነት ተሳትፎ የሚፈልገውን ፓርቲ ወይም ዕጩ ተወዳዳሪ ለመምረጥ የሚችለው በቅድሚያ በመራጭነት ሲመዘገብ ብቻ ነው፡፡

በመራጭነት ሳይመዘገብ ቀርቶ በምርጫው ዕለት መራጭ ሆኖ መቅረብ አይችልም፡፡ ስለሆነም ቦርዱ ስለመራጮች ምዝገባ መጀመር በልዩ ልዩ የብዙኀን መገናኛዎች ሲገልጽ በመከታተልና በመመዝገብ የመራጭነት መብትን በእጅ ማስገባት ያሰፈልጋል፡፡

አንድ ሰው ለመራጭነት ለመመዝገብ ወደ ምርጫ ጣቢያ በሚሄድበት ጊዜ የሚከተሉትን ሰነዶች መያዙን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡-
• በምርጫ ጣቢያው ክልል ውስጥ ነዋሪ መሆኑን የሚገልጽ መታወቂያ ወይም ፓስፖርት፤ ከነዚህ አንዱም ከሌሉት ሌሎች የማንነት መግለጫ ሰነዶችን (መንጃ ፈቃድ፣ የመኖሪያ የምስክር ወረቀት፣ በተባበሩት መንግስታት የተሰጠ የስደተኛ ካርድና የመሳሰሉት) መያዝ ይችላል፡፡

ሆኖም ካላይ የተጠቀሱት ሰነዶች ባይኖሩትም ለመመዝገብ የቀረበውን ሰው መዝጋቢዎቹ በአከባቢው ነዋሪ መሆኑን ለይተው የሚያውቁት ከሆነ ወይም በምርጫ ጣቢያው በህዝብ የተመረጡ የህዝብ ታዛቢዎች የሚያወቁት ከሆነ በቃለ-ጉባኤ ተይዞ መመዘገብ ይችላል፡፡

በተለያየ ምክንያት ራሳቸውን ችለው መመዝገብ የማይችሉ ሰዎች በረዳቶቻቸው አማካኝነት በአካል ተገኝተው መመዝገብ ይችላሉ፡፡

የመራጮች መዝገብ፤ የየዕለቱ ምዝገባ ሲጠናቀቅ በዕለቱ የመጨረሻው ተመዝጋቢ የተመዘገበበት ተራ ቁጥርና ቀን ለዚሁ በተዘጋጀ ቅጽ ላይ ከተሞላ በኋላ መዝጋቢዎችና የሕዝብ ታዛቢዎች በጋራ ይፈራረሙበታል፡፡

ይህ ድርጊት የመራጮች ምዝገባ እስከሚጠናቀቅበት ቀን ድረስ በየዕለቱ የሚከናወን ይሆናል፡፡

የመራጮች ምዝገባ በሚጠናቀቅበት ዕለትም ከመጨረሻው ተመዝጋቢ ቀጥሎ ባለው ትርፍ ቦታ ላይ መዝጋቢዎችና የሕዝብ ታዛቢዎች ተፈራርመውበት መዝገቡ ይዘጋል፡፡

የመራጮች መዝገብ በዚህ መልኩ ከተዘጋ በኋላ በምርጫ ቦርድ በተለየ ሁኔታ ካልተወሰነ በስተቀር አዲስ መራጭ ሊመዘገብበት አይችልም፡፡

የምርጫ ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ የመራጮች መዝገብ በምርጫ ጣቢያው ቅጥር ግቢ ውስጥ ለ10 ተከታታይ ቀናት በህዝብ እንዲታይ (እንዲመረመር) ይደረጋል፡፡

ምዝገባን የሚመለከት ማናቸውም ተቃውሞ በማንኛውም ሰው ወይም የፖለቲካ ድርጅት ለምርጫ ጣቢያው አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ ሊቀርብ ይችላል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ አንድ ሰው በመራጭነት እንዳይመዘገብ የሚያግደው ሁኔታ ከገጠመው ለምርጫ ጣቢያው አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ ጉዳዩን አቅርቦ ውሳኔ የማግኘት መብት አለው፡፡

በመራጭነት መመዝገብ የሌለበት ሰው ወይም መብት የሌለው ሰው ያለአግባብ ተመዝግቧል የሚል ሰው ወይም የፖለቲካ ድርጅት ተቃውሞውን ለምርጫ ጣቢያ አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ የማቅረብ እና ውሳኔ የማግኘት መብት አለው፡፡

በመራጭነት የተመዘገበ ሰው በአዕምሮ ሕመም ምክንያት ለመወሰን ብቃት የሌለው ሆኖ የተገኘ ወይም በማጭበርበር የተመዘገበ ወይም የሞተ ወይም የተፈረደበት ካልሆነ በስተቀር በማናቸውም ሌላ ምክንያት ከመራጭነት መዝገብ አይሰረዝም፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.