ኪን ኢትዮጵያ የዓድዋ ድል በዓልን ለማክበር ወደ ኬንያ ይጓዛል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ‘ኪን ኢትዮጵያ የጥበብና ባህል ቡድን’ የዓድዋ ድል በዓልን ለማክበር ዛሬ ወደ ኬንያ ጉዞ ያደርጋል አለ፡፡
የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴዔታ ነብዩ ባዬ በሰጡት መግለጫ÷ ኪን ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያን ባህል እና ጥበብ ለማስተዋወቅ በተለያዩ ሀገራት ስራዎቹን አቅርቧል ብለዋል።
‘ኪን ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት’ በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው የጥበብ ድግስ ከዚህ ቀደም በቻይና፣ በጃፓን እና በሩሲያ በስምንት መድረኮች ስራዎቹን ማቅረቡን አስታውሰዋል።
በዛሬው ዕለትም ቡድኑ የዓድዋ ድል በዓልን ለማክበር ወደ ኬንያ ጉዞ እንደሚያደርግ ገልጸው÷ የጉዞው ዓላማ የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያ ባለፈ የአፍሪካ የነፃት እና የድል በዓል ሆኖ እንዲከበር መሆኑን ገልጸዋል።
የዘንድሮው የዓድዋ ድል በዓል በመንግስት ደረጃ ከኢትዮጵያ ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ በመከበሩ የተለየ እንደሚያደርገው አስረድተዋል።
በጉዞው ኪን አትዮጵያ በባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር አስተባባሪነት በሻኩራ ፕሮዳክሽን የሚመራ ልዑካን ቡድን ከመላኩ ፈንድቃ ባህል ማዕከል ጋር በመሆን የኢትዮጵያን መልክ ለዓለም ያስተዋውቃል ብለዋል፡፡
በተለይም የባህል ልዑካኑ የኢትዮጵያ መገለጫ የሆኑትን ቡና፣ አልባሳት፣ ቁሳቁስ እና የተለያዩ ባህሎችን የማስተዋወቅ ስራ ይሰራሉ ነው የተባለው፡፡
ኪን ኢትዮጵያ በኬንያ በሚያቀርበው የዓድዋ ድል በዓል መድረክ ላይ የተለያዩ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እና የሰርከስ ቡድኖች የሚሳተፉ ሲሆን፤ በኬንያ የሚገኙ ኢምባሲዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የተለያዩ ተቋማት እና እንግዶች እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
በሲሳይ ኃይሌ