በሰው ህይወት ላይ ለውጥ የማያመጣ ልማት የተሟላ ሊሆን አይችልም – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሰው ህይወት ላይ ለውጥ የማያመጣ ልማት የተሟላ ሊሆን አይችልም አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በዛሬው ዕለት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 909 ሰልጣኞችን አስመርቋል፡፡
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ለከፋ ማህበራዊ ችግር ተጋልጠው የነበሩ ሴቶችን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አሰልጥነን በማስመረቅ ወደ ስራ አሰማርተናል ብለዋል፡፡
በሰው ህይወት ላይ ለውጥ የማያመጣ ልማት የተሟላ ሊሆን እንደማይችል ጠቅሰው÷ አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባት እንዲሁም ለዘመናት የከረሙ ስብራቶቿ የሚጠገኑባት ከተማ እንድትሆን የሚደረገው ጥረት ፍሬ እያፈራ መሆኑን ገልፀዋል።
ለነገዋ የሴቶች ማዕከል የዚህ ማሳያ መሆኑን በማንሳት፤ ማዕከሉ ከምስረታው ጀምሮ በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆነው ተስፋ ለቆረጡ እህቶች አዲስ የህይወት ምዕራፍ መክፈቻ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ማዕከሉ እስካሁን 2 ሺህ 401 ሰልጣኞችን ተመርቀው ስራ በመጀመር ህይወታቸውን በተሻለ መንገድ እንዲመሩና ለሌሎችም ምሳሌ እንዲሆኑ ማስቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡
የማዕከሉ ዋና ዓላማ ለተለያዩ ማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ እህቶች አዲስ የተስፋ ብርሃን መሆን ነው ያሉት ከንቲባዋ÷ ሰልጣኞች ስልጠናቸውን እንዲያጠናቅቁ ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ኤርጳሳ ጫላ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ሰልጣኞች ከከተማዋ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የተወጣጡና የተቋሙን የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምዘና ወስደው በማለፍ ለምረቃ የበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የማዕከሉ ተግባር የከተማ አስተዳደሩ ሰው ተኮር ስራዎች መካከል አንደኛው ማሳያ ነው ብለዋል።
በየሻምበል ምህረት