የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ያሳደረው ጫና
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመካከለኛው ምስራቅ የተከሰተው ጦርነት መራዘሙ እያንዳንዱን የዓለም ክፍል ሊነካ የሚችል የኢኮኖሚ ስጋት እየፈጠረ ይገኛል።
ሦስተኛ ሳምንቱ ላይ የሚገኘው የአሜሪካ-እስራኤል እና ኢራን ጦርነት ከመርገብ ይልቅ ይበልጥ እየተባባሰ መጥቷል።
ይህንንም ተከትሎ በሆርሙዝ ሰርጥ ያለው ወታደራዊ ውጥረት መራዘም በዓለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል አስከትሏል።
ይህም እያንዳንዱን የዓለም ክፍል የኢኮኖሚ ጫና ውስጥ እየከተተ ይገኛል።
በተለይም በእስያ፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና በአፍሪካ የሚገኙ ሀገራት ከባድ የፋይናንስ እና የማህበራዊ ፈተናዎች እየገጠሟቸው እንደሆነ ተገልጿል።
ከቀጣናዊ ግጭቶች ሊመጣ የሚችለውን የደህንነት ስጋት እና የስደተኞች ፍሰት ለመቋቋም ዝግጅት በማድረግ ላይ የምትገኘው የኢራን ድንበር ተጋሪ ተርክዬ፤ የሀገሪቱን ገንዘብ ለማረጋጋት የወለድ ምጣኔ ላይ ቅናሽ ለማድረግ ርምጃ ለመውሰድ የያዘችውን ዕቅድ ለሁለተኛ ጊዜ ለማቋረጥ መገደዷ ተነግሯል።
ይህም ሀገሪቱ ወደ ከፋ የዋጋ ግሽበት ልትመለስ ትችላለች የሚል ስጋት መፍጠሩን ሮይተርስ ዘግቧል።
ከፍተኛ የኢንዱስትሪ ምርት አምራች የሆነችው ጀርመን የነዳጅ ዋጋ መጨመር በኢኮኖሚዋ ላይ ትልቅ ጫና አሳድሯል።
ከምትጠቀመው ድፍድፍ ነዳጅ 90 በመቶን ከውጭ የምታስገባው ህንድ አሁን ባለው የዋጋ ጭማሪ ምክንያት የህንድ ሩፒ ምንዛሪ በታሪኳ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።
በተመሳሳይ ጃፓን ከምትጠቀመው ነዳጅ 95 በመቶውን ከመካከለኛው ምስራቅ የምታገኝ በመሆኗ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ በኢንዱስትሪዎቿ ላይ መቀዛቀዝ አስከትሏል።
በስሪላንካ ከፍተኛ የኃይል እጥረት በማጋጠሙ የመንግሥት ሰራተኞች በሳምንት አራት ቀን ብቻ እንዲሰሩ እና ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ሲወሰን፤ የነዳጅ አጠቃቀም በዲጂታል የፈቃድ ስርዓት ተገድቧል።
ፓኪስታን በበኩሏ ትምህርት ቤቶች ለሁለት ሳምንታት እንዲዘጉ፣ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን እና የአየር ማቀዝቀዣዎችን እንዳይገዙ ያገደች ሲሆን፣ የነዳጅ አበልንም በግማሽ ቀንሳለች።
የነዳጅ እና የምግብ ዋጋ ንረት እየተፈታተናት የምትገኘው ግብጽ፤ ከሱዊዝ ካናል የምታገኘው ገቢ መቀነስ እና የቱሪዝም ዘርፉ አለመረጋጋት የውጭ ምንዛሪ ገቢዋን ስጋት ላይ ጥሎታል።
እንዲሁም የሀገሪቱ ፓውንድ ዋጋ በዘጠኝ በመቶ ዝቅ በማለቱ በዶላር የሚከፈለውን የውጭ ዕዳዋን ለማቅለል ከፍተኛ ጫና ፈጥሮባታል።
ኢትዮጵያም ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እና ወደ ታዳሽ ኃይል በማዘንበል እንዲሁም ሌሎች የነዳጅ ቁጠባ መንገዶችን በመተግበር ችግሩን ለመቋቋም እየሰራች ትገኛለች።
በሌላ በኩል የነዳጅ እና የጋዝ ዋጋ በዓለም ገበያ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ለነዳጅ አምራች ሀገራት መልካም አጋጣሚ ቢሆንም ነገር ግን የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ እንደ ኩዌት፣ ኳታር እና ባህሬን ላሉ ሀገራት ትልቅ ፈተና ሆኖባቸዋል።
በሶስና አለማየሁ