ለበጎ ስራ የቆመ ሃውልት …
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ታሪኩ የተከሰተው ከ10 ዓመት በፊት ሲሆን በሞላ ወንዝ ውስጥ ገብታ ህይወቷ አደጋ ላይ የወደቀን አንዲት የውሻ ቡችላ ለማዳን የተደረገ የሰው ልጆች የትብብር ተግባር የበርካቶችን ልብ ያሞቀ ነበር።
ቡችላዋ ለመውጣት በማይመች ዝቅተኛ ስፍራ ባለው የወንዝ መውረጃ ውስጥ ገብታ በከፍተኛ ፍጥነት ከሚሄደው የሞላ ውሃ መውጫ አጣች፤ አሳዳሪዋ ከገባችበት ሁኔታ ሊያወጣት በቀጥታ ወደ ወንዙ ይገባል።
ነገር ግን በጣም ቁልቁለት ከሆነው የወንዝ መውረጃ መውጣት አልቻለም፤ እየዘነበ የነበረው ዝናብም ሁኔታውን የበለጠ አስቸጋሪ አድረገበት።
ቡችላዋን ለማዳን የገባው ሰውም እንዲሁ ለመውጣት ተቸገረ።
ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ አስደናቂው የትብብር ተግባር የተፈጸመው።
በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ችግር ውስጥ የገቡትን የውሻ ቡችላ እና አሳዳሪዋን በትብብር ለማውጣት ዘዴ የፈጠሩት።
በዚህም መሰረት እጅ ለእጅ ተያይዘው መስመር በመስራት ወደጉድጓዱ ተዘረጉ፤ ደርሰውም የቡችላዋን አሳዳሪ እጅ ያዙ።
አሳዳሪዋ ደግሞ ቡችላዋን ይዞ አደጋ ውስጥ ከገቡበት የወንዝ መውረጃ ጉድጓድ ለመውጣት በቁ።
ይህ የትብብር ታሪክ ከተፈጸመ እነሆ 10 ዓመታት ሆነው። ይህንን የትብብር ታሪክ የሚዘክር ሃውልትም በ10ኛ ዓመቱ ላይ የቆመለት ሲሆን፤ ተመርቆ ለእይታ ክፍት ሆኗል።
ክስተቱ የሰው ልጅ መተባበር ከቻለ የማይወጣውና የማይሻገረው ችግር እንደሌለ ያሳየ ሆኖ አልፏል።
በካዛኪስታናዊው አርቲስት ይርቦሲን ሜልዲቤኮቭ የተቀረጸው ሃውልቱ መጨረሻ ላይም ያለው የመጨረሻው ምስል እጁን ዘርግቶ የሚታይ ሲሆን ጎብኚዎች ሊይዙት እና መልካም ድርጊቱ አካል እንዲሆኑ የሚጋብዝ ነው።
ሐውልቱ አንድነትን፣ ደግነትን እና ሌሎችን መርዳትን የሚወክል ሲሆን በወቅቱ ይህንን መልካም ስራ የሰሩት ግለሰቦች ማንነት ግን እስካሁን አልታወቀም።
ይህ ቀላል የሚመስል ታሪክ ሰዎች ያለማንም ገፋፊነት የፈጸሙት የበጎነት እና የደፋርነት ተግባር ሁሌም ቢሆን በአንድነት እና በትብብር ልንኖር እንደሚገባ የሚያሳይ ነው።
አሁን ላይ በመካከለኛው ምስራቅ በተፈጠረው ቀውስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያጋጠመውን የነዳጅ እጥረት ያስከተለውን ጫና በኃላፊነት እና በትብብር መወጣት እንደሚገባ ከዚህ ህያው ሃውልት መማር ይቻላል።
በዮናስ ጌትነት