ለጫናዎች የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ግብርናው ሚናውን እየተወጣ ነው – አቶ አዲሱ አረጋ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለጫናዎች የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የግብርናው ዘርፍ ሚናውን እየተወጣ ነው አሉ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ።
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን አድአ ወረዳ የሰብል ልማት ወቅታዊ ቁመና እና እንክብካቤ እንዲሁም ሀገራዊ የሰብል ልማት ንቅናቄ ማስጀመሪያና የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል።
አቶ አዲሱ አረጋ በወቅት እንዳሉት፤ የግብርና ትራንስፎርሜሽን በመደመር እሳቤ እየተመራ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።
የግብርና ትራንስፎርሜሽን አንዱ መሠረታዊ አጀንዳ የገፀምድር፣ የከርሰምድር እና የዝናብ የውሀ ሀብትን በአግባቡ በመጠቀም ዘርፉን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ ክረምት ከበጋ ማምረት ነው ብለዋል።
በመስኖ በማልማት የተመዘገበውን እምርታ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸው፤ ለዚህም ሁሉም ባለድርሻዎች ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የግብርና ትራንስፎርሜሽን ሁለተኛው መሠረታዊ አጀንዳ ዘርፉን ወደ ሜካናይዜሽን ማሸጋገር መሆኑን ገልጸው፤ መንግሥት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ በክልሎች ከ555 በላይ የሜካናይዜሽን የዕቃ ዓይነቶች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተደርጓል ነው ያሉት።
ዘንድሮ በርካታ ማሽነሪዎች ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቅሰው፤ አጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የትራክተሮች ቁጥር 27 ሺህ፣ ኮምባይነር 12 ሺህ፣ የውሀ ፓምፕ 500 ሺህ መድረሱን እና ዘርፉ መዘመኑን ተናግረዋል።
የትራንስፎርሜሽን መሰረታዊ አጀንዳዎችን እውን በማድረግ ለጫናዎች የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የግብርናው ዘርፍ ሚናውን እየተወጣ ነው ብለዋል።
የግብርናው ዘርፍ ከእጅ ወደ አፍ አመለካከት ተላቅቆ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በማምረት ረገድ ውጤት መመዝገቡን ገልጸው፤ የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት ለዓለም የምናሳይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል።
በመሳፍንት ብርሌ