ሰሙነ ሕማማት ምንድነው? ስለሳምንቱ የተወሰነ ነገር …
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28 ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ሰሙነ ሕማማት የጾመ ሁዳዴ የመጨረሻው ሳምንት፤ የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም የሚታሰበት ሳምንት ነው።
ካህናትና ምእመናን በቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ተሰብስበው የሕማሙን ነገር የሚያወሳውን ዜማ ያዜማሉ። “ግብረ ሕማም” በመባል የሚታወቀውን መጽሐፍም ያነባሉ።
በዚህ ሳምንት በተለይ ካህናተ ቤተክርስቲያን ጥቁር ልብስ በመልበስ ኢየሱስ ክርስቶስ የደረሰበትን መከራና ስቃይ እንዲሁም የሰው ልጅ በጨለማ ግዞት ይኖር እንደነበር ለማዘከርም ጭምር ነው።
የኢየሱስ ክርስቶስ መከራና ሕማም በጽኑ እንዲታሰብ ያስተማሩት ሐዋርያት ናቸው። ለእነርሱም የነገራቸው ደግሞ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
በሰሙነ ሕማማት የኢየሱስን ሕማማት ከማሰብ ጋር በየዕለቱ በርካታ ድርጊቶች መፈጸማቸው የሚታወስበት ሳምንት ነው።
በዚሁ መሰረት:-
ሰኞ:- መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ ይባላል፦
በዚህ ዕለት ኢየሱስ ከቢታኒያ ሲወጣ ተራበ፤ ቅጠል ያለባትን በለስ ተመልክቶ ወደ በለሲቱ ቢቀርብ ከቅጠል በቀር ምንም ነገር ባለማግኘቱ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ምንም ካንቺ ፍሬ አይበላ” ማር ፲፩፥፲፬ በማለት ስለረገማት መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ ይባላል።
ይህ ዕለት አንጽሖተ ቤተመቅደስም ይባላል፡- ኢየሱስም ወደ ቤተመቅደስ ሄዶ በቤተመቅደሱ የሚሸጡትን እና የሚለውጡትን “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች” ማቴ ፳፩፥፲፫ በማለት ከቤተመቅደስ ገርፎ አስወጥቷቸዋልና።
ማክሰኞ:- የጥያቄ ቀን ይባላል፦
ሰኞ ዕለት በቤተመቅደስ ሲሸጡ እና ሲለውጡ የነበሩትን ሁሉ እየገረፈ በማባረሩ ምክንያት ለሰው ልጅ ሹመትንና ስልጣንን የሰጠ ኢየሱስ “በምን ስልጣን ይህንን ታደርጋለህ?” ማቴ ፳፩፥ ፳፫ ተብሎ በፈሪሳውያን ተጠይቋልና የጥያቄ ቀን ይባላል።
ይህም ዕለት የትምህርት ቀን ይባላል፡- በዚህ ዕለት በቤተመቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረም የትምህርት ቀን ይባላል። ሉቃ ፳፩ ፥፳፰ ፣ ማር ፲፪፥፪።
ረቡዕ ምክረ አይሁድ ይባላል፦
ረቡዕ ዕለት የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ኢየሱስን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የመከሩበትና ውሳኔ ያሳለፉበት ቀን በመሆኑ ምክረ አይሁድ ይባላል።
ወቅቱ የፋሲካን በዓል የሚያከብሩበት ቀን በመሆኑ እና ብዙ ህዝብም ይከተለው ስለነበር ሁከት እንዳይነሳ ስጋት ነበራቸው።
ነገር ግን ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ስለነገራቸው ሉቃ ፳፪፥፩-፮ ጭንቀታቸው ተወግዶ በኢየሱስ መያዝ ተስማምተዋል።
ይህም ቀን የመልካም መዓዛ ቀን ይባላል፡- ኢየሱስ በዚህ ዕለት በስምዖን ቤት ተቀምጦ ሳለ ማርያም እንተ እፍረት (ባለሽቶዋ ማርያም) ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ የአልባጥሮስ ሽቱ አምጥታ በራሱ ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባቸው ማቴ ፳፮፥፮-፯ የመዓዛ ቀን ይባላል።
በተጨማሪም ይህ ቀን የእንባ ቀን ይባላል፡-ባለሽቱዋ ሴት (ማርያም እንተ እፍረት) ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት እየለመነች በእግሩ ስር ተደፍታ በእንባዋ እግሩን አርሳለችና ማር ፲፬፥፱ የእንባ ቀን ይባላል።
ሐሙስ ፀሎተ ሐሙስ ይባላል፦
ኢየሱስ ለአይሁድ ተላልፎ ከመሰጠቱ በፊት በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ሲጸልይ በማደሩ ማቴ ፳፮፥፴፮ ጸሎተ ሐሙስ ይባላል። የደቀመዛሙርቱንም እግር በፍጹም ትህትና ዝቅ ብሎ ያጠበበት ዕለት በመሆኑም ዮሐ ፲፫፥፫-፲፩ ሕጽበተ ሐሙስ ይባላል።
ይህም ቀን የምስጢር ቀን ይባላል፡- ከሰባቱ ምስጢራት አንዱ የቅዱስ ቁርባን ምስጢር ማቴ ፳፮፥፳፮-፳፱ በዚህ ዕለት ተፈጽሟልና የምስጢር ቀን ይባላል።
በተጨማሪም የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል፡- መሥዋዕተ ኦሪት (በእንስሳት ደም የሚቀርብ መሥዋዕት) ቀርቶ ለዓለም ደኅንነት ራሱን ያቀረበበት ቀን በመሆኑ ሉቃ ፳፪፥፳ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል።
የነጻነት ሐሙስም ይባላል፡- ለኃጢአትና ለዲያቢሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱን እንዲሁም የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነም ዮሐ ፲፭፥ ፲፭ የነጻነት ሐሙስ ይባላል።
ዓርብ የስቅለት ዓርብ ይባላል፦
ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ የዋለበት ዕለት ነውና ማቴ ፳፯፥፴፭ የስቅለት ዓርብ ይባላል።
መልካሙ ዓርብም ይባላል፡- ከኢየሱስ ስቅለት በፊት በተለይም በሮማውያን ህግ የወንጀለኛ መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል በደሙ ቀድሶ የምህረት፣ የሕይወት አርማ፣ የዲያቢሎስ ድል መንሻ ስላደረገው፤ በሞቱ መልካሙ ሕይወት ስለተገኘ መልካሙ ዓርብ ይባላል።
ቅዳሜ ቅዳም ስዑር ትባላለች፦
ይህች ዕለት ከድሮ በተለየ መልኩ የኢየሱስን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረች ቅዳሜ ትባላለች።
ለምለም ቅዳሜም ትባላለች፡- ካህናቱ ለምእመናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት በመሆኑም ለምለም ቅዳሜ ትባላለች። ምዕመናንም ይህንን ለምለም ቀጤማ እስከ ትንሣኤ ለሊት በራሳቸው ላይ ያስሩታል።
ቅዱስ ቅዳሜም ትባላለች፡- ፈጣሪ በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ያረፈበት ቀን ሲሆን በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ስራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ በነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዶ ሲኦልን በርብሮ ባዶዋን ሲያስቀራት በዚያ የነበሩትን ነፍሳት የዘላለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ቅዱስ ቅዳሜ ተብላም ትጠራለች።
…………..
የሳምንቱ ትርጓሜ በሁሉም የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ተመሳሳይ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እና የካቶሊክ ክርስቲያኖች ደግሞ ሳምንቱን በተለያዩ የየዕለቱ አስተምህሮ ኹነቶች በማሰብ ያሳልፋሉ።