Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የበጀት ሸክም ከመሆን ወደ ሥራ እድል አንቀሳቃሽነት ተሸጋግረዋል – የዓለም ባንክ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የሀገሪቱ በጀት ሸክም ከመሆን ወጥተው ወደ ሥራ እድል አንቀሳቃሽነት እየተሸጋገሩ ነው አለ፡፡

ባንኩߵየበጀት ሸክም ከመሆን እስከ ሥራ እድል አንቀሳቃሽነት፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሽግግርߴ በሚል ርዕስ ባወጣው ጽሑፍ በዘርፉ የተገኘውን አስደናቂ ለውጥ አብራርቷል፡፡

እነዚህ ኢንተርፕራይዞች በሚያገኙት ገቢ ለዓመታት ራሳቸውን ማንቀሳቀስ ተስኗቸው የመንግሥት በጀት ተጨማሪ ሸክም ሆነው መቆየታቸውን ባንኩ አስታውሷል፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የነበራቸውን ከፍተኛ ገቢ እና የሃብት መጠን በአግባቡ ወደ ትርፋማነት ለመለወጥ ተቸግረው መቆየታቸው በጽሑፉ ተጠቅሷል፡፡

ኢንተርፕራይዞቹ በአግባቡ ኦዲት የማይደረጉ፣ የፋይናንስ ሥርዓታቸው በወቅቱና በተገቢው ሁኔታ የማይገመገሙ እንዲሁም ግልጽ አሰራር የጎደላቸው እንደነበሩ ነው የተመላከተው፡፡

የድርጅቶቹን መዋቅራዊ ችግር በመፍታት ወደ ውጤታማነት እንዲሸጋገሩ በተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ለሥራ እድል አንቀሳቃሽ ሞተር ለመሆን በቅተዋል ሲል ባንኩ አውስቷል፡፡

ለአብነትም በ2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ብቻ 120 ሚሊየን ዶላር (19 ቢሊየን ብር) የትርፍ ክፍፍል ለመንግሥት ገቢ ማድረጋቸውን ጠቁሟል፡፡

ይህም በመንግሥት በጀት ላይ የነበረውን ጫና በማቃለል ለደመወዝ፣ ለኤሌክትሪክ አቅርቦትና ለሕዝብ አገልግሎት የሚውል ተጨማሪ የገቢ ምንጭ መሆን መቻላቸውን አመልክቷል፡፡

የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ማሪያም ሳሊም እንዳሉት ፥ ኢትዮጵያ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን አሰራር በማዘመን በዘርፉ እድገት እያስመዘገበች ትገኛለች፡፡

ይህ ውጤት ጠንካራ የመንግሥት አመራር ከታለመለት ድጋፍ ጋር ሲጣመር ምን ሊሆን እንደሚችል አመላካች ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የተቋማትን የአስተዳደር ሥርዓት በማጠናከርና የሕዝብ ሃብትን ከልማት ግቦች ጋር በማጣጣም ለሥራ እድል ፈጠራና ለግሉ ዘርፍ መር እድገት አዳዲስ መንገዶችን እየከፈተች ትገኛለች ነው ያሉት ዳይሬክተሯ።

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.