Fana: At a Speed of Life!

ምክረ አይሁድ – የሰሙነ ሕማማት 3ኛው ቀን

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዐቢይ ጾም የመጨረሻው ሳምንት ሰሙነ ሕማማት የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን÷ የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም የሚታሰብበት ሳምንት ነው።

ካህናትና ምዕመናን በቤተክርስቲያናት ቅጥር ግቢ በመገኘት የሕማሙን ነገር የሚያወሳውን ዜማ ያዜማሉ፤ “ግብረ ሕማም” በመባል የሚታወቀውን መጽሐፍም ያነባሉ።

የኢየሱስ ክርስቶስ መከራና ሕማም በጽኑ እንዲታሰብ ያስተማሩት ሐዋርያት ሲሆኑ÷ ለእነርሱም የነገራቸው ደግሞ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

በሰሙነ ሕማማት የኢየሱስን ሕማማት ከማሰብ ጋር በየዕለቱ በርካታ ድርጊቶች መፈጸማቸው የሚታወስበት ሳምንት ነው።

በዚህም መሰረት የሳምንቱ ቀናት የየራሳቸው ስያሜ ያላቸው ሲሆን÷ ሰኞ መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ ይባላል፣ ማክሰኞ ደግሞ የጥያቄ ቀን ይሰኛል።

የሕማማት ሳምንቱ ሦስተኛዋና የዛሬዋ ቀን የምክር ቀን ትባላለች።

ቀኗ የአይሁድ ሊቃነ ካህናት ጸሐፍት በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የሞት ፍርድ ለመወሰን እንዴት እንደሚይዙት ምክር የጀመሩበት ቀን ነው፡፡

በዚህ ምክራቸው ጭንቀት የፈጠረባቸው ወቅቱ የፋሲካ በዓላቸው የሚከበርበት በመሆኑ ብዙ ሕዝብ በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት የተማረኩ፣ ተአምራቱን የሚያደንቁ ስለነበሩ ሁከት እንዳይፈጠር በመስጋት ነበር፡፡

በዚህ ጭንቀት ላይ እያሉ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ በመካከላቸው ተገኝቶ የምክራቸው ተባባሪ በመሆን ጭንቀታቸውን አስወግዶላቸዋል (ማር 14፥10)፡፡

ሄዶም ከካህናት አለቆችና ከታላላቆች ጋር እርሱን አሳልፎ እንዲሰጣቸው ተነጋገረ” (ሉቃ 22፥1)፡፡

በዚህም መሠረት ይህቺ ዕለት የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ፈሪሳውያን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ምክር የመከሩበት፣ ምክራቸውንም ያጸኑበትና ሰቅለው ይገድሉት ዘንድ የወሰኑበት ቀን በመሆኑ የአይሁድ የምክር ቀን ተብላ ትጠራለች፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.