Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ለትንሳዔ በዓል…

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ለትንሳዔ በዓል በከተማ አስተዳደር ከሚገኙ ተቋማት ጋር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል አለ የከተማዋ ስራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት።

ጽሕፈት ቤቱ ሕብረተሰቡ የትንሳዔ በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፍ የዝግጀት ስራዎች መሰራታቸውንና በዓሉ በቤት ውስጥ የሚከበር እንደመሆኑ ከአደጋ የጸዳ እንዲሆን በሰው ኃይል እና በግብዓት ዝግጅት መደረጉን አስታውቋል።

በዚህም የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በዓሉን በማስመልከት የተበላሹ የውሃ መስመሮችን የመጠገን ስራ መስራቱንና ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ዋናው መስሪያ ቤትን ጨምሮ በ10 ቅርንጫፎች ቅዳሜ ዕለት አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአዲስ አበባ ሪጅን በበኩሉ÷ የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ እንዳይኖር በቂ ዝግጅት መደረጉን በመግለጽ÷ በዋዜማና በበዓሉ ዕለት 24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጡ 15 ቡድኖች በተለያዩ አካባቢዎች በስራ ላይ እንደሚያሳልፉ አመልክቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ በዓሉ የእርድ በዓል እንደመሆኑ ተረፈ ምርቶችን በአግባቡ ከየአካባቢው ለመሰብሰብ ዝግጅት ማድረጉን ገልጾ÷ ሕብረተሰቡ ከእርድ ጋር ተያይዞ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በጽዳት መሆን እንደሚገባ አስገንዝቧል።

ተቋማቱ ሕብረተሰቡ ከበዓል ጋር ተያይዞ የሚያደርገውን ዝግጅት ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።

በበዓሉ ወቅት ለሚያጋጥሙ አደጋዎች ማሕበረሰቡ 939 ነጻ የጥሪ ማዕከል በመደወል የ24 ሰዓት አገልግሎት ማግኘት እንደሚችልም ተገልጿል።

በቅድስት ብርሃኑ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.