Fana: At a Speed of Life!

ትሕትና፣ ፍቅር እና አገልግሎት የተገለጠባት ጸሎተ ሐሙስ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ተላልፎ በተሰጠበትና የሕማማት 4ኛ ቀን በሆነው “ጸሎተ ሐሙስ” የተከናወኑ ተግባራት በክርስትና ኃይማኖት ታሪክና እምነት ውስጥ ትልቅ ስፍራ አለው።

ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ ከመያዙ በፊት ለደቀመዛሙርቱ ልዩ ልዩ ሚስጥራትን እና ትምሕርቶችን የገለጠበትና ያስተማረበት ትሕትና፣ ፍቅር እና የሐዲስ ኪዳን መሠረት ነው።

ዕለቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዘንድ በተለያዩ ስሞች የሚጠራ ሲሆን እያንዳንዳቸው የራሳቸው የሆነ ሚስጥራት እና ትርጓሜ አላቸው።

ከእነዚህ መካከል ዕለቱ “ጸሎተ ሐሙስ” በመባል የሚታወቅ ሲሆን፥ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ እስከሚያዝ ድረስ የጸለየበት ዕለት በመሆኑ ስያሜውን አግኝቷል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ለዓለም መድኃኒት አድርጎ አሳልፎ ለመስጠት ጥቂት ጊዜ በቀረው ወቅት በጌቴሰማኒ ተግቶ የጸለየበት መታሰቢያ ነው።

በዚህ ጸሎቱ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ትጋትን፣ በፈተና ወቅት ወደ እግዚአብሔር መጮኽን እና መጠጋትን አስተምሯል። (ማቴ. 26፥41)

ሁለተኛው ደግሞ “ሕጽበተ እግር” (ሕጽበተ ሐሙስ) በመባል የሚታወቅ ሲሆን የትሕትናን ጥግ ያሳየበትና ለደቀመዛሙርቱም አርአያ በመሆን እግራቸውን በውኃ ያጠበበት ዕለት መታሰቢያ ነው።

በዚህች ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ በማጠብ ማገልገልን እና ትሕትናን ያሳያበትና የትሕትና ሥርዓት አድርጎ እነርሱም በተግባር እንዲገልጡት ያስተማረበት በመሆኑ ሕጽበተ እግር የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡

“እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና” በማለት አስተምሯል፡፡ (ዮሐ.13፥14-15)

ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ለማጠብ የመጣ የንጽሕና፣ የቅድስና አምላክ መሆኑን የሚያሳይ በመሆኑ ዕለቱ “ሕጽበተ ሐሙስ” በመባል ይጠራል፡፡

ሌላኛው በዚህች ዕለት ከተከናወኑ ስራዎች መካከል የቅዱስ ቁርባን ምስጢር የተመሠረተበት እና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋውንና ደሙን የሰጠበት ዕለት በመሆኑ “ምሥጢር ሐሙስ” (ምስጢረ ቁርባን) በመባል ይጠራል።

ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር የሚታረቅበትንና የዘላለም ሕይወት የሚያገኝበትን ምስጢር የገለጠበት ነው፡፡

በዚህም በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕተ ኦሪት ማብቃቱን ገልጦ ለዓለም ድኅነት ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ምሳሌ የሚሆን ነው።

“ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና፦ እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ፦ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው” በማለት አስተምሯል። (ማቴ. 26፥26-28)

“ሐዲስ ኪዳን” (የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ) ደግሞ ሌላኛው የዕለቱ መጠሪያ ሲሆን፥ የብሉይ ኪዳን መሥዋዕት አልፎ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም የጸናው ሐዲስ ኪዳን የተመሠረተበት ዕለት በመሆኑ ይህንን ስያሜ እንዳገኘ የቤተክርስቲያኗ መምህራን ይገልጻሉ።

የኦሪት መስዋዕት (የእንስሳት ደም) አብቅቶ የአለም መድኃኒት ራሱን ለመስዋዕትነት ያዘጋጀበትና አዲስ ኪዳን የተጀመረበት፣ የኦሪት መሥዋዕት የተሻረበት የመቅደስና የምኩራብ ሥርዐት የተወገደበትና አዲስ መሥዋዕትና ሥርዐት የተተካበትም ነው፡፡

ይህ ዕለት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በተለያዩ ክንውኖችን የሚከበር ሲሆን፥ በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ዘንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየውን ትሕትናና ፍቅር ለማሰብ የእግር ማጠብ ሥርዓት ይከናወናል።

እንዲሁም የቅዱስ ቁርባን ሥርዓት የሚፈጸምበት የቅዳሴ ስርዓቱ በለሆሳስ (ብዙ የድምጽ ጩኸት ሳይሰማ) የሚፈጸምበት ዕለት ሲሆን፥ በዚህች ዕለት ሕዝበ ክርስቲያኑ በንስሐ ታጥበው ሥጋ እና ደሙን እንዲቀበሉ ቤተ ክርስቲያን በአጽንኦት ታስተምራለች፡፡

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.