Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የአፍሪካ ኩራት ነው – ፕሬዚዳንት ኤቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገሩን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ ባለፈ ለአፍሪካ ኩራት የሆነ ሠራዊት ነው አሉ የቡሩንዲ ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሊቀ መንበር ኤቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ።

ለሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የሚገኙት ፕሬዚዳንት ኤቫሪስቴ በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴርን ጎብኝተዋል።

ፕሬዚዳንቱ በመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) እና በከፍተኛ ጄኔራል መኮንኖች ደማቅ ወታደራዊ አቀባበል ተደርጎላቸው የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴርን ጎብኝተዋል።

በወቅቱም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ወታደራዊ ትብብር ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ሠራዊት የሀገሩን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ ባለፈ ለአፍሪካ ኩራት መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ሠራዊቱ ቡሩንዲ የሰላም ዕጦት ውስጥ በነበረችበት ወቅት ሰላም በማስከበር ላበረከተው ሚናና ለከፈለው መስዋዕትነት ምስጋና አቅርበዋል።

የሀገራቱ መከላከያ ሠራዊት አባላት በሶማሊያ ሰላም የማስከበር ተልዕኮ ላይ በጋራ ውጤታማ ተግባራት ማከናወናቸው ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ለቡሩንዲ ሠራዊት የስልጠና እና የተለያዩ ድጋፎችን ስታደርግ መቆየቷን ገልጸዋል።

ጉብኝቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ወታደራዊ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግርም ነው የተናገሩት።

አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) በበኩላቸው፤ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ተሀገራቱን ጥብቅ አጋርነት የሚያሳይ እንደሆነ በመግለጽ ትብብሩን ይበልጥ ለማጠናከርና ሙያዊ ልምዶችን ለመለዋወጥ ወሳኝ አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።

በመከላከያ ተቋማት መካከል ያለውን ወታደራዊ ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ፣ በወታደራዊ ኢንዱስትሪ መስኮችና በጋራ ወታደራዊ ስልጠናዎች ላይ በትኩረት ለመስራት ዝግጁነት እንዳለም አረጋግጠዋል።

ትብብሩ የሁለቱን ሀገራት የጋራ ደህንነት ከማረጋገጥ ባለፈ ለቀጠናዊ ሰላም መጠበቅ ያለውን አህጉራዊ ኃላፊነት በጋራ ለመወጣት የሚያስችል ወሳኝ ርምጃ ነው ማለታቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.