የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የአካባቢውን ልማት ለማፋጠን ትልቅ አቅም ይፈጥራል – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የበለጠ ይጠናከራሉ አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ።
የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ በወቅቱ እንዳሉት፤ የለውጡ መንግሥት የህዝቡን ኑሮ በመሰረታዊነት የሚያሻሽሉ ውጤታማ የልማት ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።
አርሲ ዞንም በክልሉ ትልቅ የመልማት አቅም ያለው ዞን መሆኑን ጠቅሰው፥ በአካባቢው ሰፋፊ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በተለይም የዞኑ አርሶ አደር አዳዲስ ኢኒሼቲቮችን ፈጥኖ በመተግበር ለሌሎችም ተሞክሮ እስከ መስጠት የደረሰ በመሆኑ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት የአካባቢውን ልማት የሚያፋጥኑ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን በልዩ ትኩረት ሲያከናውን መቆየቱንም ገልጸዋል።
በተለይም የመንገድ ተደራሽነትን እና ሽፋንን ለማሳደግ ነባር የመንገድ ግንባታዎችን ከማጠናቀቅ ባለፈ፣ የአዳዲስ አገናኝ መንገዶች ግንባታ መከናወኑን ተናግረዋል።
በጤናው ዘርፍም በርካታ ሆስፒታሎች ተገንብተው ወደ ስራ መግባታቸውን አውስተው፤ የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታ እና የመስኖ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
እነዚህ የህዝቡን ኑሮ መለወጥ ያስቻሉ ስራዎች የበለጠ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው፤ ለዚህ ስኬታማነትም ሁሉም አመራር በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ዛሬ የተመረቀው የንፋስ ኃይል ማመንጫም የአካባቢውን ልማት ለማፋጠን ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
የዞኑ ህዝብ ያገኘውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ድህነት እና ኋላ ቀርነትን ለማስወገድ መረባረብ እንዳለበትም ነው ያነሱት።
ከዚህም ባለፈ ህዝቡ ያገኘውን ሀብት በመቆጠብ ወደ ኢንቨስትመንት ዘርፍ በማሸጋገር ራሱን በዘላቂነት መለወጥ እንዳለበት አሳስበዋል።