Fana: At a Speed of Life!

በአዲሱ የወንጀል ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ የተካተቱ ዋና ዋና ነጥቦች …

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲሱ የወንጀል ሥነ ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ዘመኑን የዋጁ እና የሰብዓዊ መብቶችን አጠባበቅ የሚያጠናክሩ በርካታ የሕግ ማዕቀፎች ተካተውበታል፡፡

ከ6ዐ ዓመታት በላይ ያገለገለውን የወንጀል ሕግ የሚተካ የወንጀል ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 1410/2018 በመጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወሳል።

ከተሻሻሉ ዋና ዋና ሕጎች መካከል የዲጂታል ማስረጃዎች ዕውቅና አንዱ ሲሆን ይህም የቴክኖሎጂ ለውጥን ያገናዘበ የሕግ ማዕቀፍ ነው፡፡

ለአብነትም የቪዲዮ ምስሎች፣ የድምፅ ቅጂዎች፣ የኮምፒውተር መረጃዎች እና የማኅበራዊ ሚዲያ መልዕክቶች እንደ ትክክለኛ ማስረጃ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ሕጋዊ መሠረት ሰጥቷል።

ሌላው የተሻሻለው የምርመራ ዘዴዎች እና የሰብዓዊ መብቶችን የሚመለከት ሲሆን፤ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ሲውሉ ያላቸው መብት፣ የምርመራ ጊዜ ገደብ እና በምርመራ ወቅት ጠበቃ የማግኘት መብታቸው በግልጽ ተቀምጧል።

በዚህም መሰረት አንድ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ሲውል ጠበቃው እስኪመጣ ቃሉን ያለመስጠት መብቱ የሚጠበቅለት ሲሆን የተጠርጣሪው የምርመራ ገደብ ከአራት ወር እንዳይበልጥ በማድረግ ተጠርጣሪ ለረጅም ጊዜ በምርመራ እንዳይቆይ ያስችላል።

የተጎጂዎችን መብት በሚመለከት የወንጀል ድርጊት የተፈጸመባቸው ሰዎች በፍትሕ ሂደቱ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ፣ ጉዳታቸው የሚካካስበት መንገድ እና የሚደረግላቸው ጥበቃ ትኩረት አግኝቷል።

ሌላው የዋስትና መብትን እንደ መሠረታዊ መብት መከልከልን እንደ ልዩ ሁኔታ የሚመለከት ሕግ ሲሆን፤ በዚህም ሕጉ ግልጽ የሆኑ የዋስትና ዓይነቶችን አስቀምጧል።

እነሱም በግል ማረጋገጫ በሰው ዋስትና፣ በንብረት ዋስትና ወይም በገንዘብ ማስያዝ የሚልን አካትቷል።

ሌላኛው የምስክሮች እና የጠቋሚዎች ጥበቃ የሚመለከት ሲሆን በከባድ ወንጀሎች ላይ መረጃ የሚሰጡ ጥቆማ ሰጪዎች እና ምሥክሮች ከበቀል ወይም ከጥቃት እንዲጠበቁ የሚያስችል የሕግ ከለላ መስጠትን ይመለከታል።

በተመሳሳይ የዐቃቤ ሕግ የክስ ድርድርን በተመለከተ አንድ ተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ ጥፋተኛነቱን አምኖ ከዐቃቤ ሕግ ጋር በመደራደር ቅጣቱ እንዲቀልለት ወይም ክሱ እንዲቋረጥ የሚያስችል ሥርዓት በሕጉ እንዲካተት ተደርጓል።

በዚህም በአዋጁ ዐቃቤ ሕግ ክስ ለማንሳት የሚችልባቸው ምክንያቶችና ቅድመ ሁኔታዎች በዝርዝር ተቀምጠዋል።

የክስ ድርድር በሚመለከት ክስ ከመመሥረቱ በፊት ወይም ክስ ከተመሠረተ በኋላ ፍርድ እስከሚሰጥ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ተጠርጣሪው ወይም ተከሳሹ ጥፋተኛነቱን አምኖ ከዐቃቤ ሕግ ጋር ሊደራደር ይችላል።

የድርድር ዓይነቶችን በሚመለከት ከባድ የሆነውን ክስ ወደ ቀለል ያለ የወንጀል ዓይነት በመቀየር መደራደር እንዲሁም በቅጣት ድርድር በክሱ ላይ ተስማምቶ ቅጣቱ እንዲቀልለት መደራደር የሚል ይገኝበታል።

በዚህም በድርድሩ የተደረገው በፈቃደኝነት መሆኑን፣ ተከሳሹ መብቶቹን መረዳቱን እና ድርድሩ የሕዝብን ጥቅም የማይጎዳ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ማረጋገጥ አለበት።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ድርድሩን ውድቅ የማድረግ ሥልጣን ያለው ሲሆን በተለይም ዐቃቤ ሕግ የክስ ድርድር ሲያደርግ የወንጀል ተጎጂዎችን ፍላጎትና ስሜት ግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለበት ሕጉ ይደነግጋል።

ተጎጂው ካሳ የሚያገኝበት መንገድም በድርድሩ ውስጥ የተከካተተ ሲሆን ይህም ተከሳሹ የቅጣት ቅናሽ እንዲያገኝ ያደርጋል፡፡

በተጨማሪም ድርድሩ መንግሥት ለምስክሮች እና ለረጅም ክርክር የሚያወጣውን ወጪ ይቆጥባል፣ ተጎጂዎች ደግሞ የፍርድ ሂደቱን ሳይጠብቁ ካሳ ወይም ይቅርታ ሊያገኙ ይችላሉ።

በአጠቃላይ እነዚህ ለውጦች ፍትሕን በፍጥነት ለመስጠት እና የተጠርጣሪዎችንም ሆነ የተጎጂዎችን መብት በተሻለ ሁኔታ ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ማሻሻያዎች ናቸው፡፡

ይህም በሀገሪቱ የፍትሕ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ አፈጻጸሙም ከሕገ መንግሥቱ እና ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.