Fana: At a Speed of Life!

በአደጋ ላይ የሚገኝን ሰው አለመርዳትና የሕግ ተጠያቂነቱ …

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ መሠረት በአደጋ ላይ የሚገኝን ሰው አለመርዳት የወንጀል ተጠያቂነትን ያስከትላል።

በሕጉ መሰረት ሰውን የሚያስጠይቁ የወንጀል ተግባራት በሁለት የሚከፈሉ ሲሆን፤ የመጀመሪያው አታድርግ የተባለን ነገር በማድረግ የሚመጣ የወንጀል ተጠያቂነት ነው።

ሁለተኛው ደግሞ አድርግ በሚል በሕግ የተጣለን ግዴታ ባለማድረግ የሚመጣ ተጠያቂነት ነው።

በዚህ መልኩ አድርግ በሚል በሕግ የተጣለን ግዴታ ማለትም አደጋ ላይ የሚገኝን ሰው የመርዳት ግዴታ በሕጉ ተቀምጧል።

በዚህም መሰረት አደጋ ላይ የሚገኝን ሰው አለመርዳት ከ6 ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም በመቀጮ እንደሚቀጣ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 575 ንዑስ ቁጥር 1 ላይ ተደንግጓል።

በተጨማሪም በድንጋጌው ንዑስ ቁጥር 2 ስር ደግሞ ቅጣቱን የሚያከብዱ ሁኔታዎች ተመላክተዋል፡፡

ይህም በማናቸውም ሁኔታ ወይም ዘዴ በተጎጂው ላይ ጉዳቱን ያደረሰው ሰው ተጎጂውን ለመታደግ ወይም ለመርዳት የሙያ ወይም የውል፣ የሕክምና ሌላ ሕጋዊ ግዴታ ያለበት ከሆነ ቅጣቱ ከ1 ወር እስከ 2 ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት ወይም መቀጮ ይሆናል።

በዋናነት ተጎጂውን ለመታደግ ወይም ለመርዳት የሙያ ሕክምና ሌላ ሕጋዊ ግዴታ ያለበት ሰው በቂ ባልሆነ ምክንያት በምንቸገረኝነት፣ በቸልተኝነት፣ በጥላቻ፣ በንቀት ወይም ያለአግባብ ገንዘብ በመፈለግ በማናቸውም ተመሳሳይ ምክንያት አስፈላጊ የሆነውንና በሙያ ተግባሩ ሊያደርገው የሚገባውን እርዳታ ማለትም የህክምና አገልግሎት ሳይሰጥ (ሳይፈፅም) የቀረ እንደሆነ በንዑስ ቁጥር 2 መሰረት ቅጣቱ የሚከብድበት ሁኔታ ይኖራል።

ይሁንና ግዴታ የሚጣልበት ሰው ያለበት ኃላፊነት አደጋ ላይ የሚገኝን ሰው በቀጥታ ራሱ ከመርዳት ባለፈ በተዘዋዋሪም ቢሆን የመርዳት ግዴታ አለበት።

በአጠቃላይ ማንኛውም ሰው ሰውን ለመርዳት የሚያስችል ሁኔታ ላይ እስከተገኘ ድረስ አደጋ ላይ የሚገኝን ሰው መርዳት ወይም ደግሞ ሌሎች እንዲረዱት ማስቻል ተገቢነት እንዳለው በወንጀል ሕጉ ተመላክቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.